24 ህዳር 2023

ፒካዱስ በረፈደ ቁጥር እየገረረች ሁሉንም የምትተናኮሰውን ፀሐይ ለመሸሽ የምትነቃው ማልዳ ነው። የምትችለውን ያህል ከውና ረፋዱ ላይ መልሳ ትተኛለች። ዳግም በንቁነት ወደ መታተር የምትመለሰው አመሻሹን ዘጠኝ ሰዓት ላይ ጉልበተኛዋ ፀሐይ ስትደካክምላት ነው። ከጂቡቲ ዋና ከተማ 12 ኪሎ ሜትር ያህል ተጉዘው ወደ ፒካዶስ ሲመጡ በስተግራ በኩል የኢትዮጵያን ሰሌዳ የለጠፉ የከባድ መኪና ተሽከርካሪዎች ተደርድረው ይታያሉ። እነዚህ የደረቅ ጭነት የሚያመላልሱ መኪኖች በመቶዎች የሚቆጠሩ ናቸው። እነዚህ ለወደብ አልባዋ ኢትዮጵያ ስንቋን ወደ አገር ውስጥ፤ አረንጓዴ ወርቋን እና ሌሎች የግብርና ምርቶቿን ደግሞ ከአገር ውጪ ዶላር ፍለጋ የሚያመላልሱ መኪኖች የሚሰባሰቡት፣ ፒካዱስ ጂቡቲ ላይ ነው። አጠገባቸው የኢትዮጵያ ትራንስፖርት ባለሥልጣን ተገቢውን አገልግሎት ለመስጠት እንዲያስችለው ቢሮ ከፍቷል። ፊት ለፊታቸው ላይ ደግሞ የተዘረጋው በአብዛኛው በኢትዮጵያውያን የተያዘው የምግብ ቤት ንግድ ነው። ምግብ ቤቶቹ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ይወዘወዛሉ። ወሬያቸው የሚደምቀው በአገር ልጅ ቋንቋ ነው። ገዢ እና ሻጭ የሚዋዋለውም በኢትዮጵያ ብር ነው።

አንጻራዊ ነጻነት የማገኝበት ቦታ ነው

በፒካዱስ ከጂቡቲያውያን ይልቅ ኢትዮጵያውን በዝተው ይታያሉ። በእርግጥ ሁሉም ለማለት በሚያስደፍር መልኩ በሕገ ወጥ መልኩ ነው የሚኖሩት። በሌሎች የጂቡቲ አካባቢዎች ከሚኖሩት በተሻለ ግን ከፖሊስ ጋር በየዕለቱ ድብብቆሽ መጫወት እዚህ የለም። ጂቡቲን የእጄ መዳፍ ያህል አውቃታለሁ የምትለው ጂጂነጠላ በነጻነት ለብሼ የምንቀሳቀሰው ፒካዱስ ነውትላለች። ፖሊስ ፀጉረ ልውጥ ነሽ ብሎ የማያሳድዳት፣ በአንጻራዊነት በዚህች በትንሿ የኢትዮጵያውያን መናኽሪያ ፒካዱስ ነው። እዚያም ከጂቡቲ የሥራ ቋንቋዎች ከአረብኛ እና ከፈረንሳይኛ ይልቅ አማርኛ፣ ኦሮምኛ እና ትግርኛ በስፋት ይነገራሉ። በአካባቢው የሚገኙ ንግድ ቤቶች ዙሪያቸውን በቆርቆሮ የተሠሩ እና ሸራ የለበሱ ናቸው። ከወሎ እንደመጣ የሚናገረው እና በፒካዱስ ከስድስት ዓመት በላይ የኖረው መሐመድ ሳኒ፣ በዚህ አካባቢ75 በመቶ በላይ ሹፌር ነው የሚታየውይላል። ቀሪዎቹ በጉልበት ሥራ የሚተዳደሩ፣ በንግድ ቤቶች ውስጥ የሚሠሩ ወይንም ደግሞ የስደት እግር ጂቡቲ ጥሏቸው ፒካዶስን ለመሸሸጊያነት የመረጡ ናቸው። ለዚህ ማሳያው ደግሞ ዕድሜው 20ዎቹ መጀመሪያ ላይ የሚገመተው ወጣት ነው። ሙራድ [ለዚህ ታሪክ ሲባል ስሙ የተቀየረ] እስከ አስራ አንደኛ ክፍል ድረስ መማሩን ይናገራል። ቤተሰቡ በኦሮሚያ እና በሶማሊ ክልሎች መካከል ግጭት በተቀሰቀሰበት ወቅት ከጂግጂጋ ተፈናቅለው ገላን ከተሙ። እርሱም ትምህርቱን የተወሰነ ከገፋ በኋላ ለጫማ ንግድ የሚሆን ገንዘብ ከወንድሙ ተቀብሎ ወደ ጂቡቲ ተሰደደ። ጂቡቲ ግን ውጣ አስቀረችው። በትንሿ ኢትዮጵያ መካከል ሰምጦ ቀረ። የፒካዱስ ደጀኖች የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ናቸው። እነርሱ ከሌሉ የፒካዱስ እስትንፋስ ይቋረጣል። ምግብ ቤቶቹ እነሱን አስባው ካልሆነ ለማን ብለው፣ ማንን አምነው ደጃቸውን ይከፍታሉ?

ሙራድ ይህንኑ ሲያጠናክርተሳቢዎቹ ባሉበት አካባቢ በርካታ ልጆች ይገኛሉይላል። በእርግጥ እነዚህ ከኢትዮጵያ የተሻለ ኑሮን ፍለጋ ወደ ጂቡቲ የመጡ ታዳጊዎች፣ ሙራድን ጨምሮ ሥራ አጥተው የተገኘችውን ምንዳ ከሹፌሮች ለማግኘት ወዲያ ወዲህ ይላሉ። ሙራድም ቢያንስ ቢያንስ ከአገር ልጆች ጋር አፉን በፈታበት ቋንቋ እየተጨዋወተ፣ የፒካዱስ ጓዳ ያበሰለውን ሽሮም ሆነ ዳቦ በሻይ እየቀመሰ የስደትን ሕይወት ይመራል። መሐመድ ደግሞ በፒካዱስሁሉ በእጅ ሁሉ በደጅ ነውይላል። አክሎምየዋጋውን ነገር ግን አታንሱት፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨሰ ነውሲል ያማርራል። የኢትዮጵያውያን እጆች የሚያዘጋጇቸውን ምግቦች የሚቋደሱት ኢትዮጵያውያን ብቻ አይደሉም፤ በአካባቢው የሚኖሩ ሶማሌያውያንም እንጂ። እንደ እርሱ አባባል ከሆነ የዛሬን አያድርገው እና የኢትዮጵያ ብር ከዚህ ቀደም ጠንካራ የመግዛት አቅም ነበረውበፒካዱስ።

በኢትዮጵያ ሙዚቃ አንገቷን የምትሰብቀው ፒካዱስ

ፒካዱስ በፈረንሳይኛ 12 ማለት ነው ይላሉ በስፍራው ያገኘናቸው። እነዚሁ ኢትዮጵያውያን ቢካዱስ፣ ሚካዱስም በማለት ይጠሩታል። አገሬው ደግሞ PK-12 (Piquer à douze) ሲል ይጠሯታል። ትርጉሙን አጥብቆ ለጠየቀ እርግጡን የሚናገር አይገኝም። ቀጥታ ፍቺው አስራ ሁለት ምልክቶች እንደ ማለት ነው ይላሉ። እርግጠኛ ሆኖ መናገር የሚቻለው ከጂቡቲ ከተማ 12 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የዋናውን መንገድ ግራ እና ቀኝ ይዛ የምትገኝ መንደር መሆኗን ብቻ ነው። በፒካዱስ የሚታየው የከባድ መኪና አሽከርካሪ ቁጥር ስፍር ቁጥር የለውም።እነርሱን ተከትሎ ደግሞ ሌላው ኢትዮጵያዊ ከትሟል።ስፍር ቁጥር የሌለው ሹፌር ይመጣል፣ ከዚህ ሰፈር ውጪ ግን አይወጡም። እዚህ አገር ፈረንሳይኛ፣ አፋርኛ እና ሶማልኛ ይነገራል። የእኛ ሹፌሮች ላይ የቋንቋ ክፍተት ስላለ ከመጡ ከዚህ ከፒካዱስ አይወጡምየሚለው መሐመድ ሳኒ ነው። በእርግጥ ፒካዱስ ከደረሱ ከአገር ርቄያለሁ እና ናፍቆቱ አስቸገረኝ የሚሉት ነገር የለም። ቡናው እስከ እነ ትኩስ መዓዛው እየተቆላ፣ እጣኑ እየተትጎለጎለ፣ ትኩስ ሽሮ በወፍራም እንጀራ እንዲሁም ሌሎች አገር ቤት የሚያገኟቸው ነገሮች ሁሉ ያገኛሉ። የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ደግሞ ለመኝታ መኪናቸውን እንደሚመርጡ ይናገራሉ።ዋጋው ይወደድ ይሆናል እንጂ የምንፈልገውን እናገኛለንያሉን ምግብ ቤቶች ውስጥ ቁጭ ብለው ቡና እየጠጡ ካርታ ሲጫወቱ ያገኘናቸው የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ናቸው። ወደ መዝናኛ ቤቶቿ የገባ በተከፈተው ቴሌቪዥን የኢትዮጵያ ዜናን ሊመለከት፣ በጎጃምኛ የባሕል ዘፈን አልያም በትግርኛ ሙዚቃ ትከሻውን ሊነቀንቅ ይችላል። በየምግብ ቤቱ ሲገቡ ሹፌሮች ሰብሰብ ብለው ሲጨዋወቱ ይመለከታሉ። በምግብ ቤቶቹ፣ በሸቀጣ ሸቀጥ ሱቆች፣ በመጋዘኖች ውስጥ ሁሉ ኢትዮጵያውያን ይታያሉ። ንግድ ቤቶቹ በተለይ ደግሞ ምግብ ቤቶቹ በባለቤትነት የተያዙት በኢትዮጵያውያን ነው። አስተናጋጆቹም ቢሆኑ የአገር ልጆች ናቸው። ሹፌሮች እዚህም እዚያም ሰብሰብ ብለው ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት ካርታ እየተጫወቱ አልያም ሌላ የጋራ የሆነ ጉዳይ እየከወኑ ነው።

ብርሃን በፒካዱስ ቡና እያፈላች ስትሸጥ ነው ያገኘናት። በፒካዱስ ሁለት ዓመት ብትቆይም በቡና ንግድ ላይ ከተሰማራች ግን ገና ስድስት ወሯ ነው። አንድ ስኒ ቡና በሃያ ብር ትሸጣለች። ደንበኞቿ ከኢትዮጵያ የሚመጡ ሹፌሮች ናቸው። ቡናዋን እየቆላችእዚህ ያለው ሐበሻ እና ሱማሌ፣ስፕሪስነው፤ ቅልቅልትላለች አካባቢውን ስትገልጸው። ብርሃን ሽሮ ሠርታ፣ ቡና አፍልታ በምትነግድበት ፒካዱስ ኑሮን አሸንፋለሁ ብላ ብትወጣምበኪራይ ነው ገንዘቤን የምጨርሰውትላለች። በፒካዱስ ሽሮ 160 እስከ 200 የኢትዮጵያ ብር፣ ውሃ 70 እስከ 100 ብር፣ ጥብስ 400 ብር ገደማ፣ አንድ ስኒ ቡና ደግሞ 20 ብር ይገኛል። ረዥም ጊዜ የተቀመጡ ኢትዮጵያውያን ለክፉ ጊዜ ብለው እድር አቋቁመዋል። በአቅራቢያቸው ደግሞ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያንን ተክለዋል።  በፒካዶስ መንገድ ዳር በስፋት የሚታየው የልብስ ገበያ

ለግብይት የኢትዮጵያን ብር የምትጠቀመው ፒካዱስ

ፒካዱስ የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ወደ ኢትዮጵያ ይዘው መሄድ የሚፈልጉት ሁሉ በገፍ የሚቀርብበት ስፍራ ነው። ከሽቶ እስከ ወተት፣ ከልብስ እስከ ስኳር፣ ከሳሙና እስከ ሻምፖ እዚህ ይሸመታል። ደፈር ያለ ሹፌር የተወሰነውን የቤቱን አስቤዛ እዚህ ያደርጋል። ኢትዮጵያ ይወደዳል ወይንም አይገኝም ያሉትን ሁሉ እዚህ ለመሸመት ግን የጂቡቲ ፍራንክ መያዝ አይጠበቅም። የኢትዮጵያን ብር ከያዙ ያለ ችግር ይገበያያሉ። በእርግጥ መንገድ ዳር ቁጭ ያሉ ሴቶች የኢትዮጵያ አንድ መቶ ብርን 150 የጂቡቲ ፍራንክ ይዘረዝራሉ። በፒካዱስ የገበያ መንገዶች መተላለፍያ ላይ ገንዘብ ለመዘርዘር በፕላስቲክ ወንበር ቁጭ ብለው የሚታዩት ሶማሊያውያን ሴቶች ናቸው። እነዚህ ገንዘብ መንዛሪዎች በአገሬው ቋንቋ፣ ሳሪፍሌ (sarifley) ይባላሉ። ሴቶቹ በመንገድ የሚያልፍ ደንበኛቸውን፣ በዐይናቸው እያባበሉ ለመዘርዘር የሚፈልገው ማን እንደሆነ ለመለየት ይሞክራሉ። እነዚህ በትልቅ ቦርሳቸው በርካታ ብር፣ ዶላር፣ ዩሮ እና የጂቡቲ ፍራንክ የያዙ መንዛሪዎች ብቻቸውን ከመሆን ይልቅ ሁለትም ሦስትም ሆነው መቀመጥን ይመርጣሉ። እንደ የከባድ መኪና ሹፌሮቹ አባባል ከሆነ ከዚህ በፊት የኢትዮጵያ ብር ጠንካራ ስለነበረ የሚያስፈልጋቸውን ነገር ለመሸመት ርካሽ ሆኖ ያገኙት ነበር። አሁን ግን የኢትዮጵያ ብር ምንዛሬ እየወደቀ መምጣት በጂቡቲ የሚሸምቷቸው ነገሮችን ውድ አድርጎባቸዋል።

ፒካዱስ ከኢትዮጵያ ድንበር 200 ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ ያለች ቢሆንም፣ መንገዱ አስቸጋሪ በመሆኑ ብቻ በጋላፊ በኩል ሁለት ቀን፣ በድሬዳዋ በኩል ደግሞ አንድ ቀን እንደሚፈጅ በስፍራው ያነጋገርናቸው የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ነግረውናል። ይህችን ከኢትዮጵያ ድንበር 200 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው ትንሽ ከተማ፣ ሰባት ዓመት በከባድ መኪና አሽከርካሪነት ሲመላለስ የሚያውቃት ሁሉ እንደተለዋወጠች ይናገራል። በየጊዜው ሞቅ ደመቅ እያለች፣ ንግድ ቤቶቿ እየጨመሩ፣ የኢትዮጵያውያን እንዲሁም የከባድ መኪና ተሽከርካሪዎች ቁጥርም እያደገ ሄዷል።ቤቱ ብቻ ሳይሆን ዋጋውም እንደዚያው እየጨመረ መጥቷልይላል ከጓደኞቹ ጋር ካርታ እየተጫወተ ያገኘነው የከባድ መኪና አሽከርካሪው ኪሮስ፣ የዋጋ መወደድን ሲናገር።

 

በፒካዱስ ገበያ ስፍራ ተቀምጠው ገንዘብ የሚዘረዝሩ ሴቶች የኢትዮጵያ ከባድ መኪና አሽከርካሪዎች በጂቡቲ ፒካዱስ በትንሹ ከሰባት እስከ 10 ቀናት እንቆያለን ብለው ይገምታሉ። በተለያየ ምክንያት ጭነት ከጠፋ ደግሞ እስከ ሁለት ወር ድረስ ሊቆዩ ይችላሉ። ያኔ ታድያ የያዟት የአበል ብር ተሟጣየኮቴ የምንከፍለውን እስክንበላ ድረስ የምንቆይበት ጊዜም አለይላል የከባድ መኪና አሽከርካሪው ኪሮስ። በዚህ ወቅት ደግሞ ኢትዮጵያዊ መተዛዘን፣ እርስ በእርስ የመደጋገፍ ባህል ብቅ ይላል። ገንዘብ ጨርሻለሁ ለሚል አሽከርካሪኢትዮጵያዊ ከሆነ ሹፌሮች ብቻ ሳይሆን ባለ ሆቴሎች ሁሉ ይሰጣሉይላል ኪሮስ። በፒካዱስ የኢትዮጵያ ባንኮች የሉም። ስለዚህ ገንዘብ የጨረሰ ሹፌር፣ የኢትዮጵያ ጋላፊ ድንበር እስከሚደርስ ሌሎች ሹፌሮች ይዘው የመጡትን ገንዘብ በመካፈል ይቆያል። ኪሮስም ከሌሎች ሹፌሮች ጋር ወደ ጀመረው ካርታ ተመልሷል። ብርሃን የምትቆላውን ቡና ጨርሳ ምግብ ለማዘጋጀት ደፋ ቀና ትላለች።  ሙራድ ብቻ ስለ ወደፊቱ ምን ማድረግ እንዳለበት አያውቅም። እንዲሁ ዝም ብሎ በትንሿ ኢትዮጵያ ነዋሪዎች መካከል ተሸሽጎ ያገኘውን በልቶ መሽቶ ይነጋል። በዚህ ያለ ሕጋዊ ሰነድ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች የሙራድ ዓይነት ነገ ነው ያላቸው።  ቀን ያመጣውን እንደ አመጣጡ ተቀብሎ መኖር! ሕይወት ግን በፒካዱስ የከባድ መኪና አሽከርካሪዎቹን ፍሰት ተከትላ ትገማሸራለች።

ኢትዮ ካብ ስለሚሰጠው አገልግሎት ለማወቅ ድህረገጻችንን www.ethiocab.com ይጎብኙ

Driver application ለማውረድ  http://driver.ethiocab.com  እንዲሁም Customer application ለማውረድ  http://user.ethiocab.com     

አብረን ሰርተን ትርፋችንን እንካፈል  !!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *