30 ህዳር 2023
በታይም መጽሔት ከዓመቱ የአየር ንብረት ተጽዕኖ ፈጣሪ የዓለማችን 100 ሰዎች መካከል አንዱ በመሆን ተመርጧል፤ ቅዱስ አስፋው። የአካባቢ ቴክኖሎጂ ኩባንያ የሆነው ኩቢክ መሥራች እና ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሆነው ቅዱስ ‘የአየር ንብረት መሪዎች’ ተብለው ዝርዝሩ ውስጥ ከተካተቱት የዓለም የቢዝነስ መሪዎች አንዱ ነው። ቅዱስ ያቋቋመው ድርጅት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የፕላስቲክ ምርቶች ወደ ዝቅተኛ የካርበን ሕንጻዎች በመቀየር ከአካባቢ ለማስወገድ የሚሠራ ነው። እነዚህ ለረጅም ጊዜ የሚዘልቁ እና ተመጣጣኝ የሆኑ ፕላስቲኮች ከትምህርት ቤቶች እስከ ጤና ተቋማት፣ ከመኖርያ ቤት እስከ መጋዘኖች ለመገንባት እየዋሉ ነው። ኩቢክን በአውሮፓውያኑ 2021 የመሠረተው ቅዱስ፤ ታይም መጽሔት “የቢዝነስ እሴት በመፍጠር የአየር ንብረት ለውጥን በመዋጋት ረገድ ከፍተኛ መሻሻል ለማምጣት” እየሠሩ ከሚገኙት መካከል የመረጠው ሲሆን፣ በዚህ ዝርዝር ውስጥ የተካተቱ ግለሰቦች የአየር ንብረት ለውጥን ለመዋጋት ያደረጉት ጥረት “ሊለኩ የሚችሉ ስኬቶችን” ስላስመዘገቡ ነው ብሏል። በዚህም ቅዱስ አስፋው የአየር ንብረት ለውጥን ለመዋጋት ላከናወነው ተጨባጭ ተግባር በዓለም ዙሪያ ካሉ የዓመቱ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰዎች መካከል አንዱ ሆኖ ለመመረጥ በቅቷል። ቀደም ሲል ቅዱስ ለዩኒሴፍ የቴክኖሎጂ እና የፈጠራ ሥራዎችን በመምራት የህፃናትን ሕይወት ለማሻሻል የተከናቀኑ ሥራዎችን መርቷል። ከዚህ ባሻገር ቅዱስ ከዓለም ባንክ፣ ጉግል እና ከሌሎችም ጋር ሠርቷል። ቢቢሲ ከአየር ንብረት ሥራ ፈጣሪው ቅዱስ አስፋው ጋር ያደረገው ቆይታ እንደሚከተለው ይቀርባል።
ቢቢሲ፡ ታይም መጽሔት በአየር ንብረት ዙሪያ ሊለኩ የሚችሉ ስኬቶች አስገኙ ካላቸው 100 ተጽዕኖ ፈጣሪዎች መካከል አንዱ አድርጐ አጭቶሀል። እንኳን ደስ አለህ፤ በቅድሚያ የአየር ንብረት ሥራ ፈጠራ ‘climate entrepreneur’ ምንድን ነው?
ቅዱስ፡ አመሰግናለሁ፤ የአየር ንብረት ሥራ ፈጠራ በቢዝነስ ደረጃ፤ አንድ ሰው የአየር ንብረት ለውጥ መታገል ይችላል የሚል ዓይነት ሰው ነው። አንዳንዶች በኢንዱስትሪነት ገንዘብ አሰባስበው ወደ ቢዝነሶች ኢንቨስት የሚያደርጉ አሉ፤ አንዳንዶች ደግሞ በባህሪ ለውጥ ተሟጋች ሆነው እንዴት አድርገን የሰውን ባህሪ መለወጥ እንችላለን ብለው የሚያስቡ አሉ። ሌሎች ደግሞ ተቋም መሥርተው የአየር ንብረት ለውጥ ለመዋጋት በስፋት የሚሠሩ አሉ።
ቢቢሲ፡ ከ100 ሰዎች መካከል አንዱ ሆነህ አንድትመረጥ ያደረገህ እና የምትመራው ድርጅት ኩቢክ የሚያከናውናቸው ሥራዎች ምንድን ናቸው?
ቅዱስ፡ ኩቢክ ስንመሠረት ብዙ ዓይነት ቁጥሮች አይተን ነው። የመጀመሪያው ከ30 ዓመት በኋላ 70% የዓለም ነዋሪ ከተማ ውስጥ ነው የሚኖረው። በከተማ ደግሞ ሦስት ትልልቅ ችግሮች ማስወገድ ይሞክራል። አንደኛ የቆሻሻ አያያዝ (waste management) ነው። የሕዝብ ቁጥር ሲጨምር ቆሻሻ ስለሚኖር፣ በአግባቡ መወገድ አለበት። ሁለተኛው ደግሞ የከተማ አስተዳደር ያን ሁሉ ነዋሪ እንዴት በሥርዓት ማኖር እችላለሁ የሚል ሀሳብ ነው የሚያየው። ይሄ ደግሞ በጣም ትልቅ ችግር ነው፤ ለምን ሕዝብ በበዛ ቁጥር ኑሮ ይወደዳል – በተለይ የቤት ዋጋ። በዚህ ምክንያት አብዛኛው አቅም የሌለው ሰው ምቹ ባልሆነ ቦታ ውስጥ ነው የሚኖረው። ሦስተኛው ግን የአየር ንብረት ለውጥ ነው። ከተማ ሲባል ለአየር ንብረት ለውጥ አንደኛ አስተዋጽኦ የሚያደርግ ነገር ነው። ያም የሚሆንበት ብዙ ምክንያቶች አሉ፤ ግን አንደኛው በሪልስቴት እና ግንባታ ላይ ያለው ትኩረት ነው። ከተሞች ውስጥ ደግሞ የምናየው ነገር ቢኖር ትልልቅ ሕንጻዎችን ለመገንባት ብዙ አሸዋ እና ሲሚንቶ መጠቀምን ነው። እነዚህ ለአካባቢ በጣም በካይ ናቸው። [እነዚህ የግንባታ ቁሳቁሶች] ለአየር ንብረት ለውጥ ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ከመሆናቸው የተነሳ ሪልስቴት 40% አስተዋጽኦ ያደርጋል። ስለዚህ ኩቢክን ስንመሠርት ይሄን ሁሉ እንዴት አድርገን መፍታት እንችላለን ከሚል ነው። ስለዚህ የፈጠርነው ቴክኖሎጂ የፕላስቲክ ቆሻሻን እያወጣን ወደ ግንባታ እቃዎች እየለወጥን፤ በዝቅተኛ ብክለት በርካሽ ዋጋ ቤቶች እንዲገነቡ የሚያስችል ነው። በመሆኑም ከፕላስቲክ ቆሻሻ ዝቅተኛ ዋጋ እና ዝቅተና ብክለት ያላቸውን የግንባታ ቁሳቁሶች ነው የምንሠራው።
ቢቢሲ፡ የአየር ንብረት ለውጥ የተፈጥሮ ዑደት የሚያስከትለው እንጂ የሰው ባህሪ ላይ የምናየው መዘናጋት አይደለም የሚሉ ክርክሮች አሉ። አንተ ቀለል ባለ ቋንቋ የአየር ንብረት ለውጥን እንዴት ነው የምታስረዳው?
ቅዱስ፡ የአየር ንብረት ለውጥ በጣም የተወሳሰበ፣ ከአቅም በላይ የሆነ ጽንሰ–ሐሳብ ነው። የአየር ንብረት ለውጥን አንድ ሰው በዕለት ከዕለት ሕይወቱ አይመለከተውም ወይም አያስበውም። እኔ ሰውን በቀላል መንገድ ነው የማስረዳው፤ በተለይ ለምንድን ነው የእናንተን ምርት መጠቀም ያለብን ቢሉኝ ‘እስቲ የግንባታ ቦታ ላይ ሂዱ እና ተንፍሱ’ እላቸዋለው፤ ምክንያቱም ያ ስለ ብክለት ቶሎ ያስረዳል። ያም ሆኖ ግን፤ እኛ ንግድ ላይ ነው ያለነው ሰው የእኛን ምርት (ኩቢክ) የሚገዛው ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ለመዋጋት አይደለም። የእኛን ምርት በዝቅተኛ ዋጋ መግዛት ስለሚችል፣ [በእነዚህ ምርቶች] ቶሎ ቤት መገንባት ስለሚችልበት እና ብዙ ማሽነሪ ስለማያስፈልገው ነው። በዚያ መንገድ ነው የምናስረዳው። ነገር ግን በጊዜ ሂደት ድርጅቱ እየተስፋፋ የአየር ንብረት ለውጥ እንዴት መዋጋት እንደሚቻል እናያለን።
ቢቢሲ፡ በዚህ ዘርፍ እንድትሰማራ ምክንያት የሆነህ ነገር ምንድን ነው?
ቅዱስ፡ የሦስት ልጆች አባት ነኝ፤ ስለዚህ ሁሌም ስለእነሱ ሕይወት ማሰብ አለብኝ። ምን አይነት ኑሮ እንደሚኖሩ ማሰብ አለብኝ። ስለዚህም የሚኖሩበት ዓለም ምን ሊመስል ይችላል ብዬ ሳስብ በጣም የሚያሰጋኝ አይነት ደረጃ ላይ ደርሷል። ይህም በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የተነሳ ነው። ስለዚህ አባታቸው በምን ያስታውሱ ብዬ ሳስብ ‘አንድ ነገር ለመለወጥ ሞክሯል’ ብለው እንዲያስቡ ነው የምፈልገው። ኩቢክንም በምሠራበት ጊዜም ይህን ሁሌ አስበዋለሁ። ከዚያ ውጪ ግን ኩቢክን ከመመሥረቴ በፊት ዩኒሴፍ ውስጥ ስሠራ ብዙ ነገር አይቻለሁ። በዚህም ከአካባቢ ፕላስቲክ እየሰበሰብን እንዴት ትምህርት ቤቶችን መገንባት እንደምንችል አይቮሪኮስት ውስጥ ፕሮጀክት ጀምረን ነበር። ያን ጊዜ ነው ይህ ቴክኖሎጂ እንዴት ተስፋ ሰጪ እንደሆነ በደንብ የተመለከትኩት።
በጣም ስኬታማ ነበረ፤ ብዙ ትምህርት ቤቶችን ሠራን፤ እንዴት አድርገን ቆሻሻ መልቀም እንደምንችል አየን፣ ሳይንሱንም አየን፤ እንዴት አድርገን ብክለትን መቀነስ እንደምንችል ተመለከትን። ከዚህ በኋላ ምን ይመጣል ብዬ ሳስብ ግን በትምህርት ቤት፣ በኮትዲቯር መቅረት የለበትም፤ ይሄን በደንብ አስፋፍተን ከተማን የሚለወጥ መሆን አለበት ብዬ ነው ኩቢክን የጀመርኩት።
ቢቢሲ፡ እስከ አሁን በኩቢክ ሥራዎች ውስጥ የኢትዮጵያ ሕዝብ ምን ያህል የፕላስቲክ ምርት እንደሚጠቀም ማወቅ ተችሏል?
ቅዱስ፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞ በደንብ መሥራት የጀመርነው ባለፈው ዓመት ነው። ኢትዮጵያ የ120 ሚሊዮን ሰዎች መኖሪያ ናት፤ ስለዚህ በቀን ውስጥ አንድ ሺህ ቶን [አንድ ሚሊዮን ኪሎ] የሚሆን የፕላስቲክ ቆሻሻ ይወጣል። አብዛኛው ደግሞ እንደ አዲስ አበባ ካሉ ከተሞች የሚወጣ ነው። ይህ ምርጫ ኖሮን ሳይሆን ሰው በበዛ ልክ እንደዚህ አይነት ችግር ይከሰታል። ዋናው ነገር ግን ይሄንን ፕላስቲክ እንዴት አድርገን ወደ ውሃ፣ ወደ ፍሳሽ ማስወገጃ እና ወደ እርሻ ቦታዎች እንዳይገባ አድርገን ማስወገድ አለብን የሚለው ነው።
ቢቢሲ፡ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የቆሻሻ አወጋገድ ልምድ በምን ደረጃ ይገኛል?
ቅዱስ፡ ልክ እንደ ሌሎቹ አገራት ብዙ ነገር ይቀረናል። ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ያየሁት አንድ ነገር፤ ባህላችን አንዳንድ ነገሮችን መልሶ ጥቅም ላይ እንዲውል (recycle) ለማድረግ ይሞክራል። እኔ ሳድግ ሁሌ በሰፈር የሚያልፍ “ቆራሊዮ” የሚባል ሰው አለ። ያ ሰው ለእኔ የተጠቀምነውን ፕላስቲክም ይሁን ጀሪካን እየለወጠ እንደገና ጥቅም ላይ የሚያውል ነው። ግን አዲስ አበባ ደግሞ ከ10 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ያላት ናት።
ቢቢሲ፡ ግን እርግጥ ስለ አየር ንብረት ለውጥ መጨነቅ አለብን?
ቅዱስ፡ እንዳልኩት እኔ እዚህ ውስጥ የገባሁት ልጆቼ ወደፊት ሊገጥማቸው የሚችለው ነገር አሳስቦኝ ነው። ግን ዝም ብለን የአየር ንብረት ለውጥ ብለን በጽንሰ–ሐሳብ ካስቀመጥነው ደግሞ እጅግ በጣም ሰፊ ከመሆኑ የተነሳ ከየት እንደምንጀምር ግራ ያጋባል። አሁን እኛ ይሄን ጉዳይ በሁለት መንገድ ነው ያየነው። አንድ በግንባታ ላይ ያለውን ብክለት እንዴት መቀነስ እንችላለን፤ ሁለተኛው ደግሞ ፕላስቲክ በሚከማችበት ጊዜ ይቃጠላል ወይም እዚያው በስብሶ ብዙ መርዛማ ነገሮች ይፈጥራል። ይህ ለአየር ንብረት ለውጥ አስተዋጽኦ ማድረጉ አይቀርም። ታዲያ ይህን እንዴት አድርገን መቀነስ እንችላለን የሚል ትልቅ ለውጥ የሚያመጣ መንገድ ነው።
ቢቢሲ፡ በኢትዮጵያ የግንባታ ዘርፍ ትልቁ ኢንዳስትሪ መሆኑን ይታወቃል፤ በየጊዜው በርካታ ግንባታዎች በየቦታው ይታያሉ። ኩቢክ የሚያመርታቸው ምርቶች ደግሞ የግንባታ ኢንዱስትሪዎች የሚጠቀሟቸውን ግብዓቶች መተካትን ነው። በዚህ መካከል ሊፈጠር የሚችለውን ችግር መፍታት አልከበዳችሁም? እንዴት ማሳመን ቻላችሁ?
ቅዱስ፡ በሁለት መንገድ አልከበደንም አንድ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ በግንባታ ግብዓት ላይ ትልቅ ጉድለት አለ። በዓመት የሲሚንቶ የፍላጎት እና አቅርቦት ልዩነት ወደ 5 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ይሆናል። ያን ለመሙላት ያለው ፍላጎት ትልቅ ነው። ሁለተኛው ነገር ደግሞ የግንባታው ዘርፍ ለምን እኔ የሠራሁት አይሆንም ሳይሆን እንዴት አድርገን በዋጋ፣ በኢኖቬሽን የተሻሻለ እናድርግ የሚል ኢንዳስትሪ ነው። እኛ የምንፈልገው አማራጭ የሆኑ ግብዓቶችን ማቅረብ ነው። ያ በሚቀርብበት ጊዜ ወደፊት ሲሚንቶ ላይ የሚሠሩ ምናልባት ከእኛ ጋር መተባበራቸው አይቀርም። እኛም ቢዝነስ መግደል ሳይሆን ቢዝነስን አበረታትን በሌላ ቴክኖሎጂ እንዲስፋፉ ነው የምንፈልገው። ይህ በሚሆንበት ጊዜ ነው ከተማንም፣ ዓለምንም መለወጥ የምንችለው። ይህንን ግን ኩቢክ ለብቻው ይሠራዋል ብለን አናምን።
ቢቢሲ፡ እያንዳንዳችን በአየር ንብረት ለውጥ ላይ አስተዋጽኦ እያደረግን እንደሆነ በምንድን ነው ማወቅ የምንችለው?
ቅዱስ፡ አንዳንዴ፤ በግል በጣም ከባድ ነው። ለምሳሌ ነዳጅ የሚጠቀም መኪና [ለአየር ንብረት ለውጥ] አስተዋጽኦ እያደረገ ነው። ግን አማራጭ ከሌለ መኪና እንጠቀማለን። ነገር ግን በምንችለው መንገድ እና አቅም መቀነስ ከተቻለ ትልቅ ነገር ነው። ከዚያ ውጪ ያን ለማካካስ ለዓለም የሚጠቅም ነገር መሥራት አስፈላጊ ነው። እና ሁላችንም ከአንድ ቦታ መጀመር ከቻልን ትንሽ የምንለው ነገር ትልቅ ሊሆን ይችላል። እኛም ኩቢክን ስንጀምር ሁሉንም ነገር እንፈታለን ብለን ሳይሆን፣ በራሳችን መንገድ ከጀመርን ከአንድ ዓመት በኋላ እንደ እኛ ሌሎች የበኩላቸውን ቢሠሩ ለውጥ ማምጣት ይቻላል።
ቢቢሲ፡ ወደፊት ማየት የምትፈልገው ምንድን ነው?
ቅዱስ፡ እኔ ማየት የምፈልገው በዚህ ዘርፍ ላይ ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፍ ቢዝነሶች በሚሰማሩበት ሥራ ላይ እንዴት አድርገው ዓለምን ሊጠቅም የሚችል ሥራ መሥራት እንችላለን ብለው ማሰብ አለባቸው። ነገር ግን እሳቤያቸው የአጭር ጊዜ ከሆነ እነሱ ባይጎዱም ከእነሱ በኋላ የሚመጣው ትውልድ ይጐዳል። ስለዚህም ዘላቂነት እና የአየር ንብረት እንቅስቃሴ ሁሌም አጀንዳቸው ውስጥ መገኘት አለበት። ሁሉም ተቋማት ትኩረት ሊሰጡት እና ተጠያቂነት መኖር አለበት። ያ ካልሆነ በዘርፉ ቴክኖሎጂ ላይ ፈጠራ እና መሻሻል አይመጣም፣ የሥራ መበረታታ እና መስፋፋት አይኖርም።
ኢትዮ ካብ ስለሚሰጠው አገልግሎት ለማወቅ ድህረገጻችንን www.ethiocab.com ይጎብኙ
የ Driver application ለማውረድ http://driver.ethiocab.com እንዲሁም የ Customer application ለማውረድ http://user.ethiocab.com
ኑ አብረን ሰርተን ትርፋችንን እንካፈል !!