የአውስትራሊያው ጄይኮ አሉላ የብስክሌት ቡድን ጋላቢ የነበረው ብስክሌተኛ ፅጋቡ ግርማይ ከብስክሌት ሕይወት ራሱን አገለለ።
ከ24 ዓመታት በኋላ ኢትዮጵያን በኦሊምፒክ መድረክ የወከለው ፅጋቡ በተለያዩ ዓለም አቀፍ መድረኮች በግሉ እና ሃገሩን ወክሎ ተወዳድሯል።
የአውስትራሊያው ጄይኮ አሉላ በኢንስታግራም ገፁ በለቀቀው መልዕክት ፅጋቡን ላበረከተው አስተዋፅዖ አመስግኖ በቀሪ ሕይወቱ መልካም እንዲገጥመው ተመኝቷል።
በዓለም አቀፉ የሳይክሊንግ ማዕከል ተመልምሎ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ የዓለም አቀፍ ብስክሌት ሕይወቱን የጀመረው ፅጋቡ ለተለያዩ ቡድኖች ተወዳድሯል።
ፅጋቡ፤ ጥቁሮች ብዙም በማይታዩበት ዓለም አቀፉ የብስክሌት ውድድር መድረክ ደምቀው ከታዩ ጥቂት ጥቁር አፍሪካዊያን መካከል ነው።
ፅጋቡ ጉምቱ በሚባሉት የቱር ደ ፍራንስ፣ ጂሮ ዲ ኢታሊያ እና ቩዌልታ ኤ ኢስፓና ተሳትፏል።
በ32 ዓመቱ የብስክሌት ሕይወት በቃኝ ያለው ፅጋቡ ለ11 ዓመታት ያክል በፕሮፌሽናል ብስክሌት ውድድር ተሳትፏል።
ፅጋቡ በሃገር ቤት እና በአህጉረ አፍሪካ ውድድሮች ተሳትፎ 12 ጊዜ ያሸነፈ ሲሆን ሶስት ጊዜ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ውድድር አሸናፊ ሲሆን በ2015 የአፍሪካ ሰዓት ውድድር አሸናፊ ነበር።
ፕሮፌሽናል ጉዞ
ፅጋቡ ገብረማርያም፤ መቀለ 17 ቀበሌ ነው ተወልዶ ያደገው። 10 ልጆችን ካፈራው የአቶ ገብረማርያም ግርማይ ቤተሰብ፤ ስድስተኛ ልጅ ነው። አባቱ፤ ጎሚስታ ቤት ስለነበራቸው እሱና ታላቅ ወንድሙ በብስክሌት መመላለስ የጀመሩት ገና ከልጅነታቸው ነው።
አባቱ አቶ ገብረማርያም ግርማይም በ1960ዎቹ፤ ትግራይ ውስጥ እውቅ ብስክሌተኛ ነበሩ። ታላቅ ወንድሙ ሰለሞንና፤ የፅጋቡ ታናሽ ወንድም ቅዱስም እንዲሁ ብስክሌተኞች ናቸው።
የፅጋቡ የመጀመርያው የብስክሌት አሰልጣኙ፤ ታላቅ ወንድሙ ነበር። ከዚያ ቀጥሎ ትራንስ ኢትዮጵያ የብስክሌት ቡድንን ተቀላቀለ።
የዓለም አቀፉ የብስክሌት ማዕከል አሰልጣኝ ዣን ፒዬር፤ የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሽን አንድ ተወዳዳሪ እንዲያጩ ጥሪ ሲያቀርብ ከተመረጡ ብስክሌተኞች መካከል አንዱ ፅጋቡ ነበር።
ከዚያ በኋላ ወደ ደቡብ አፍሪካ በማቅናት በማዕከሉ የአፍሪካ ቅርንጫፍ ልምምድ ማድረግ ጀመረ።
ቀጥሎ የዓለም አቀፉ የብስክሌት ማዕከል ዋና መቀመጫ ወደሆነችው ስዊትዘርላንድ በማቅናት በአውሮፓውያኑ 2012 የመጀሪያ ቡድኑ የሆነው ኤምቲኤን-ኹቤካን ተቀላቀለ።
በሚቀጥለው የውድድር ዘመን የፕሮ ኮንቲነንታል ፈቃድ ካገኘ በኋላ ላምፕሬ-ሜሪዳ፣ ትሬክ-ሴጋፍሬዶ እና ጄይኮ አሉላ ተወዳድሯል።
በ2013 በፕሮፌሽናል ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ በተሳተፈበት የቱር ደ ታይዋን ውድድር አምስተኛውን ዙር በማሸነፍ የብስክሌት ሕይወት በድል ጀምሯል።
ፅጋቡ ታላላቅ በሚባሉት የብስክሌት መድረኮች ማለትም ቱር ደ ፍራንስ፣ ጂሮ ዲ ኢታሊያ እና ኤ ኢስፓና በመሳተፍ ከጥቂት ጥቁር አፍሪካዊያን መካከል አንዱ ነው።
በየዓመቱ በሚዘጋጀው የቱር ደ ፍራንስ ውድድር ሶስት ተከታታይ ጊዜ የተሳተፈው ፅጋቡ ከዚህ ግዙፍ ውድድር ባለፈ በቱር ደ ስዊዝና በቱር ኦፍ ኦማንም ተሳትፏል።
የቡድን አጋሮቹ ፅጋቡን ጠንካራ የተራራ ብስክሌተኛ እንደሆነ የሚገልጡ ሲሆን በቡድን ውድድር ለቡድኑ መሪ ትልቅ እርዳታ በማድረግ ይታወቃል ይሉታል።
“ብስክሌት እንደኔ የሌሎችን ሕይወት እንዲቀይር እፈልጋለሁ”
ፅጋቡ ብስክሌት መንዳት ካቆመ በኋላ ትልቁ ሕልሙ ተሰጥዖ ያላቸውን ታዳጊዎች ወደ ዓለም አቀፍ መደረክ ማምጣት እንደሆነ በተደጋጋሚ ይናገራል።
በ2019 ጄይኮ አሉላ አሊያም ግሪን ኤጅ ሳይክሊንግ የተሰኘው የብስክሌት ቡድን ፌስቡክ ገፁ ላይ ባጋራው አንድ ቪድዮ ፅጋቡ ከስምንት ዓመቱ ጀምሮ ከጎሚስታ አባቱ ጋር ይሠራ እንደነበር ተናግሯል።
“አባቴ እና ታላቅ ወንድሜ ብስክሌተኞች ነበሩ። የነሱን ዱካ ተከትየ ነው እኔም ወደ ብስክሌት ዓለም የመጣሁት። ከሀገር ውጭ ደግሞ አለቤርቶ ኮንታዶር ትልቅ አርአያ ሆኖኛል። በ2007 [በአውሮፓውያኑ] ቱር ደ ፍራንስ ሲያሸንፍ ተመልክቻለሁ” ይላል።
ቬሎ ከተሰኘው የብስክሌት ዜናዎችን ከሚያቀርብ ድረ-ገፅ ጋር ባለፈው ጥር ቆይታ ያደረገው ፅጋቡ “ብስክሌት የኔን ሕይወት እንደቀየረው ሁሉ የሌሎችን ሕፃናት ሕወይት እንዲቀይር እሻለሁ” ሲል ተናግሮ ነበር።
“በኔ ጊዜ የሚያግዘኝ አልነበረም” የሚለው ፅጋቡ እሱ ግን የብስክሌት ተሰጥዖ ያላቸውን ታዳጊዎች በማገዝ ለታላቅ ደረጃ እንዲደርሱ ማገዝ እንደሚፈልግ ይናገራል።
ከትግራይ ክልል የመጣው ሌላኛው የጄይኮ አሉላ ተወዳዳሪ ሃገስ ወላይ ፅጋቡ አርአያ እንደሆነው ይናገራል። ፅጋቡ ደግሞ በሃጎስ እንደሚኮራ አውርቶ አይጠግብም።
ፅጋቡ በጠቅላላው ስምንት ‘ግራንድ ቱር’ በመባል የሚታወቁ ውድድሮች ላይ ተሳትፏል።
ከሚቀጥለው የአውሮፓውያኑ ዓመት ጀምሮ ፅጋቡ በብስክሌት ውድድር ባናየውም ወደ ሃገር ተመልሶ ታዳጊዎችን በመልመል ስሙ ሊነሳ እንደሚችል ግን እሙን ነው።
ኢትዮ ካብ ስለሚሰጠው አገልግሎት ለማወቅ ድህረገጻችንን www.ethiocab.com ይጎብኙ
የ Driver application ለማውረድ http://driver.ethiocab.com እንዲሁም የ Customer application ለማውረድ http://user.ethiocab.com
ኑ አብረን ሰርተን ትርፋችንን እንካፈል !!