![](https://ethiocab.com/wp-content/uploads/2023/11/c0a658b0-7809-11ee-b315-7d1db3f558c6.jpg.webp)
1 ህዳር 2023
እአአ 2004 ላይ ኪማኒ ማሩጌ የቀለም ትምህርት ፍለጋ በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ሲመዘገቡ የዓለማችን በዕድሜ የገፉ አዛውንት ተማሪ ሆኑ። የ84 ዓመቱ አዛውንት ኬንያዊ ወታደር ነበሩ። የእንግሊዝ ቅኝ ግዛት አስተዳደርን ተዋግተዋል። በልጅነት የትምህርት ዕድልን የተነፈጉት ኪማኒ፣ የኬንያ መንግሥት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርትን ነጻ ሲያደርግ ማንበብ እና መጻፍ የምችልበት አጋጣሚ ይህ ነው በማለት ነበር በስተርጅና ከዘራቸውን ተደግፈው ወደ ትምህርት ቤት ያቀኑት። የኪማኒ የቀድሞ መምህርት ስለተማሪያቸው ያጋሩት ታሪክ ታዲያ በመላው ዓለም ሰዎችን ያነሳሳ ሆኗል። ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት በፈረንጆቹ 2003 ላይ ርዕሰ መምህርት ጄን ኦቢንቹ የቢሯቸው በር ሲንኳኳ የቀጣይ ዓመት የትምህርት ዕቅድ እያወጡ ነበር። ከወጭ ሆነው በር ሲያንኳኩ የነበሩት ኪማኒ ማሩጌ ነበሩ። ኪማኒ ለርዕሰ መምህሯ መንግሥት ነጻ ባደረገው የትምህርት ዕድል ተጠቃሚ መሆን እንደሚሹ ይነግሯታል። ርዕሰ መምህርቷ ግር ተጋቡ። ምክንያቱም የ84 ዓመቱን አዛውንት ከሕጻናት ጋር እንዲማሩ መፍቀድ እንዳለባቸው እርግጠኛ አልነበሩም።“ትምህርት ለመከታተል ዕድሜዎ በጣም ገፍቷል ብለን አሰናበትናቸው። ተመልሰው አንዳይመጡ በማሰብ በ2004 (እአአ) ትምህርት ሲጀመር መጥተው ይጠይቁ ብለን ሸኘናቸው” ይላሉ ርዕሰ መምህርቷ። ኪማኒ ግን እንዲህ በቀላሉ ተስፋ የሚቆርጡ አልነበሩም።“ትምህርት 2004 (እአአ) ላይ ሲጀመር፤ የትምህርት ቤቱን ዩኒፎርም ለብሰው ቢሮዬ ተገኙ። ደብተር እና እርሳስም በቦርሳቸው ይዘው ነበር” በማለት ጄን ከ20 ዓመታት በፊት የነበረውን ሁኔታ ያስታውሳሉ።
ኪማኒ ወደ ትምህርት ቤት እንዲያቀኑ የገፋፋቸው ትልቁ ምክንያት መጽሐፍ ቅዱስ በራሳቸው ለማንበብ የነበራቸው ጽኑ ፍላጎት ነው። ኪማኒ ወደ ትምህርት ቤት ቢያመሩ በትምህርት ቤቱ ያለች ሴት ማንበብ እና መጻፋ እንደምታስተምራቸው ራዕይ መመልከቻቸውን ለርዕሰ መምህሯ ነገሯት።“መማር የፈለጉት በራሳቸው መጽሐፍ ቅዱስ ለማንበብ ስለሚሹ ነው። እናም በራዕይ ማንበብ እንዲችሉ የምትረዳቸው የተመለከቷት ሴት እኔ ነበርኩ” ይላሉ ጄን። በመጨረሻ ርዕሰ መምህሯ የ84 ዓመቱን አዛውንት ተማሪ አድርገው ኤልዶሬት ተብሎ በሚታወቀው የኬንያ ግዛት በሚገኘው የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት መዘገቧቸው። ኪማኒ ዩኒፎርማቸውን ጥንቅቅ አድርገው ለብሰው በሰዓታቸው ትምህርት ቤት ይገኛሉ። በእረፍት ሰዓት በከዘራቸው ተደግፈው ከክፍል ተማሪዎቻቸው ጋር ወዲያ ወዲህ እያሉ ይጫወቱም ነበር። የኪማኒ ትምህርት ቤት መግባት በኬንያ መነጋገሪያ ሆነ፤ መነጋገሪያ ብቻም አልነበረም። አዛውንቱ ለበርካቶች መነሳሳት ሆኑ።“ለኬንያ ልጆች እና ለተቀረው ዓለም ትምህርት ከምንም በላይ፤ ጸጋ ከመሆንም በላይ መሆኑን ማስተማር እፈልጋለሁ። እውነተኛ ባለጸግነት የሚመጣው ሲማሩ ነው” ብለው እአአ 2006 ላይ ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናግረው ነበር። ሁሉም ግን የአዛውንቱን ተነሳሽነት በበጎ አልተመለከተውም። በተለይ የተማሪዎች ወላጆች። አዛውንት ተማሪ ከልጆቻቸው ጋር በአንድ ክፍል ውስጥ ሆኖ ሲማር መመልከታቸው አልተዋጠላቸውም ነበር።
ጄን አዛውንቱ እንዲማሩ በመፍቀዳቸው በወላጆች ቅሬታ ቀርቦባቸው ወደ ሌላ ትምህርት ቤት እንዲዘዋወሩ ተደረጉች። ጄን እጅ ሳይሰጡ ለአዛውንቱ ተማሪ ዕድል መሰጠት እንዳለበት ተከራክረው ወደ ቀደመ የሥራ ገበታቸው ተመለሱ። እዚያም ኪማኒ ማንበብ እንዲችሉም ማስተማርን ተያያዙት። ኪማኒም ለውጥ አመጡ። አንድ ቀን መጽሐፍ ቅዱስ አንስተው የዮሐንስ ወንጌል ቁጥር 3፡16 አነበቡ። “ያ ያነበቡት የመጀመሪያው ጥቅስ ነው። እግዚአብሔር ለእኛ ሃጢያት ሲል አንድ ልጁን ለሞት ስለመላኩ የሚገልጽ ጥቅስ ነው። ይህን ጥቅስ ሲያነቡ ዐይኖቻችን እምባ አቅርረው ነበር።”ጄን ኪማኒ የተመለከቱት ራዕይ እውነት እንደሆነ እንዳመኑ ይገልጻሉ።
![](https://ethiocab.com/wp-content/uploads/2023/11/8c90ccd0-780a-11ee-b315-7d1db3f558c6.jpg.webp)
ዓለም አቀፍ እውቅና
ከዚያ የጄን እና ኪማኒ ዝና ከኬንያዋ ኤልዶሬት ግዛት አልፎ ኒው ዮርክ ደረሰ። እአአ 2005 ላይ ኪማኒ እና ጄን ወደ ኒው ዮርክ ተጋብዘው በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ስብሰባ ላይ መልዕክት አስተላለፉ። ኪማኒ በኒው ዮርክ ቆይታቸው በዝነኛው ቢጫ የተማሪዎች አውቶብስ ውስጥ ሆነው ሰላምታ እያቀረቡ በታይም ስኩዌር ጎዳና ላይ ሽር ሲሉ የሚያሳይ ምስል በወቅቱ ተጋርቶ ነበር። ኪማኒ በመንግሥታቱ ድርጅት ተገኝተው ባስተላለፉት “መልዕክት የመማር ዕድሉ ያላቸው በሙሉ ትምህርት ቤት እንዲሄዱ መልዕክቴ በመላው ዓለም ላሉ በሙሉ እንደሚደርስ ተስፋ አድርጋለሁ” ብለው ነበር። ኪማኒ እአአ 2009 ላይ ሕይወታቸው አልፏል። የማይሞት ስማቸውን ግን ተክለው አልፈዋል። የኪማኒ ስም በድንቃ ድንቅ መዝገብ ላይ ሰፍሯል። ከሕልፈታቸው በኋላም ሕይወታቸውን የሚዘክር “ዘ ፈርስት ግሬደር” [የአንደኛ ክፍል ተማሪው] የሚል ፊልም ተሰርቶላቸዋል። ኪማኒ ሕይወታቸው ካለፈ በኋላ ፕሮሶላ ሲቲኤኒ የተባሉ የ85 ዓመት አዛውንት ኪማኒን አርዓያ በማድረግ ካዋለዷቸው የልጅ ልጆቻቸው ጋር ለመማር አንደኛ ክፍል ገብተው ነበር። አዛውንቷ 99 ዓመት ደፍነው ሕይወታቸው እስካለፈበት እሰከ አአአ 2022 ድረስ ተማሪ የነበሩ ሲሆን፣ ይህም ዓለም በዕድሜ ትልቋ የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪ ሳያደርጋቸው እንደማይቀር ይታመናል።
ኢትዮ ካብ ስለሚሰጠው አገልግሎት ለማወቅ ድህረገጻችንን www.ethiocab.com ይጎብኙ
የ Driver application ለማውረድ http://driver.ethiocab.com እንዲሁም የ Customer application ለማውረድ http://user.ethiocab.com
ኑ አብረን ሰርተን ትርፋችንን እንካፈል !!