አዛውንቱ የበርካታ መገናኛ ብዙኃን ባለቤት ሮበርት ሙርዶክ ከፍቅረኛቸው ጋር ትዳር ለማድረግ ቀለበት ማሰራቸው ተሰማ።
የ92 ዓመቱ ሙርዶክ ከሩሲያዊቷ የ67 ዓመት የሞሌኪዩላር ባዮሎጂስት ኤሌና ዡኮቫ ጋር ለወራት በፍቅር ቆይተዋል።
ሰርጉ በያዝነው ዓመት ካሊፎርኒያ በሚገኘው የሚሊየነሩ የተንጣለለ አዳራሽ እንደሚካሄድ ይጠበቃል።
ይህ ከሆነ የዕድሜ እና የንዋይ ባለፀጋው ሙርዶክ ለአምስተኛ ጊዜ ጋብቻ ሊያደርጉ ነው ማለት ነው።
ዜናውን ያወጣው ኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጣ እንደሚለው ሰርጉ ሰኔ የሚካሄድ ሲሆን ተጋባዦች ደግሞ የጥሪ ወረቀት ደርሷቸዋል።
አውስትራሊያ የተወለዱት ሙርዶክ በአውሮፓውያኑ 2023 ከአን ሌዝሊ ስሚዝ ጋር ቀለበት አስረው ሳለ ነው ከአሁኗ ዕጮኛቸው ጋር የፍቅር ግንኙነት እንደጀመሩ የተነገረላቸው።
ሙርዶክ ባለፈው ዓመት ነበር ፎክስ ኤንድ ኒውስ ኮርፕ ከተሰኘው ተቋማቸው ሊቀ-መንበርነት የወረዱት።
ጥንዶቹ የተገናኙት ሮበርት ሙርዶክ ወደ ቀድሞዋ ቻይናዊት ሚስታቸው ዌንዲ ዲንግ ግብዣ ተጠርተው ሄደው ሳለ ነው።
የሙርዶክ የቀድሞ ሚስቶች አውስትራሊያዊቷ የበረራ አስተናጋጅ ፓትሪሺያ ቡከር፣ ስኮትላንዳዊቷ ጋዜጠኛ አና ማን፣ ዴንግ እና አሜሪካዊቷ ሞዴል እንዲሁም ተዋናይት ጄሪ ሆል ናቸው።
የአሁኗ ዕጮኛቸው ዡኮቫ ከዚህ ቀደም ከሩሲያዊው የነዳጅ ቢሊየነር አሌክሳንደር ዡኮቭ ጋር ትዳር ነበራቸው።
የዡኮቫ እና ዡኮቭ ሴት ልጅ ዳሻ ደግሞ የቼልሲ እግር ኳሰ ባለቤት የነበሩት ሮማን አብራሞቪች ሚስት ነበረች።
ሮበርት ሙርዶክ በአውሮፓውያኑ 1969 የዩናይትድ ኪንግደም ጋዜጣ የሆኑትን ኒውስ ኦፍ ዘ ዎርልድ እና ዘ ሰን ጋዜጣን በመግዛት ነበር ወደ ሚድያው ዓለም የተቀላቀሉት።
ወደ አሜሪካ ደግሞ መጥተው ዘ ኒው ዮርክ ፖስት እና ዎል ስትሪት ጆርናልን በመግዛት የመገናኛ ብዙኃን ግዛታቸውን አስፍተዋል።
በ1996 ፎክስ ኒውስን አቋቋሙ። ፎክስ ኒውስ አሁን በአሜሪካ ቁጥር አንድ ተመልካች ያለው የዜና ጣቢያ ነው።
ሙርዶክ በ2013 ኒውስ ኮርፕ የተሰኘው ግዙፍ ተቋም ያቋቋሙ ሲሆን፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሀገራዊ እና ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ባለቤት ናቸው።
ሙርዶክ ባለፈው መስከረም ነው ሊቀ-መንበርነት በቃኝ ብለው ሥልጣኑን ለልጃቸው ላኽላን ያስረከቡት።
ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ እንደሚለው ሙርዶክ አዲስ ሚስት ማግባታቸው ቢዝነሳቸውን አያመሳቅለውም። ምክንያቱም ገንዘባቸው በአራቱ ታላላቅ ልጆቻቸው ስም ነው ያለው።
በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ ብቻ ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤ ለተጨማሪ መረጃ ድህረ ገጻችንን ይጎብኙ። https://ethio-amazon.com/
ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon
ምንጭ ፡-BBC NEWS