![](https://ethiocab.com/wp-content/uploads/2023/10/3013d490-6c55-11ee-9f48-b1a13a11d5b8.jpg.webp)
ከጥቂት ሳምንታት በፊት በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ መነጋገርያ የነበረው ጉዳይ የዶ/ር ናርዶስ አዱኛ ከቤት መጥፋት ነበር። በወቅቱ ከተመረቀች ዘጠኝ ወር የሆናት ዶ/ር ናርዶስ ‘የምትወዳቸውን ሁለት ልጆቿን ጥላ ጠፋች’ የሚለው ወሬ በርካቶች የተለያዩ መላምት እንዲሰጡ አድርጓቸዋል። ከዚያ በኋላ ዶ/ር ናርዶስ ጠፋች ከተባለችበት ስትመለስ፣ የሰጠችው ቃለ ምልልስ ላይ ለመሰወሯ ምክንያቱ ከሰባት ዓመታት ከባድ የሕክምና ትምህርት በኋላ ተመርቃ ሥራ ማጣቷ የፈጠረባት ድባቴ መሆኑን ተናግራለች።
ዶ/ር ናርዶስ በአዲስ አበባ ተቀጥሮ ለመሥራት ብቻ ሳይሆን የነጻ አገልግሎት ለመስጠት ባመለከተችባቸው ሁሉ የሚቀበላት አለማግኘቷን በወቅቱ ተናግራ ነበር። የሕክምና ባለሙያዎች ከፍተኛ እጥረት ካለባቸው አገራት መካከል አንዷ በሆነችው ኢትዮጵያ፣ የጤና ባለሙያዎች ሥራ ያጣሉ የሚለው መባሉ ለብዙዎች መቀበል የሚከብድ ጉዳይ ከሆነ ዓመታት ተቆጥረዋል። ስሙ አንዳይጠቀስ የፈለገ የአዲስ አበባ ነዋሪ የሆነ እና ለዓመታት መንግሥታዊ ባልሆነ ድርጅት ውስጥ ሲሠራ የቆየ ሐኪም እንዳለው በከተማዋ እና በክልሎች መካከል ለሐኪሞች የሚሆን የሥራ ዕድል ላይ ልዩነት መኖሩን አለ። ይህ ሐኪም ለዓመታት በሠራበት መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ውስጥ የኮንትራት ጊዜው ማብቃቱን ተከትሎ፣ ለወራት ሥራ ፍለጋ ላይ እንዳለ ቢናገርም፣ ያለ ሥራ እንዲቆይ ያስገደደው በሙያው ሥራ ማጣቱ ሳይሆን በግል ምርጫው ምክንያት እንደሆነ ይናገራል። አዲስ አበባ ውስጥ ያለው ተጨባጭ ሁኔታ “በአገሪቱ ውስጥ ሐኪም ሥራ አጥ እየሆነ ነው አያስብልም” የሚለው ይህ ዶክተር፣ ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ሐኪሞች እና ሌሎችም ሙያተኞች ወደ አዲስ አበባ ከተማ እየፈለሱ መሆኑን ጠቅሷል። ይህ የሕክምና ባለሙያ ሁኔታውን ከሌሎች አካባቢዎች ጋር ሲነጻጸር፣ ሐኪም አዲስ አበባ ውስጥ ሥራ የማግኘት ዕድሉ አናሳ እየሆነ መምጣቱን ያሳያል ይላል። “ለምሳሌ የአማራ ክልል ሐኪም እየፈለገ ነው። የኦሮምያ ክልል በአሁኑ ጊዜ እንኳ ሐኪም በመቅጠር ላይ ይገኛል። ይህንን ስትመለከት አገሪቱ ውስጥ ሐኪም ሥራ አጥ እየሆነ ነው ማለትን አስቸጋሪ ያደርገዋል።
በ2011 ዓ.ም. ዋቻሞ ዩኒቨርስቲ ገብቶ ሚድዋይፍ ማጥናት የጀመረው ታልዬ፣ የጤናው ሁኔታ ሲፈታተነው ለቤተሰቡ ቀረብ ለማለት በሚል ወደ ደብረ ብርሃን ዩኒቨርስቲ ቀይሮ ሦስቱን ዓመት ተምሯል።በአካባቢያችን ዩኒቨርስቲ ገብቶ መማር እና መመረቅ ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው ነገር ነው የሚለው ታልዬ፣ በተለይ እርሱ ደግሞ ጤና ማጥናቱ የአካባቢው ማኅበረሰብ ዐይኑን እንዲጥልበት እንዳደረገው ይገልጻል።ታድያ የቤተሰቦቹ ተስፋ እውን እየሆነ እንደሆነ ያሰበው ታልዬ፣ አንድም ቀን በጤና ተመርቄ ሥራ አጣለሁ ብሎ አያስቦ አያውቅም ነበር። አራት ዓመታትን ያለ እንቅልፍ እና እረፍት በትጋት እየተማረ ማሳለፉን የሚናገረው ታልዬ፣ ለዚህ ምስክሬ እጅግ በጣም ከፍተኛ የሚባልን አጠቃላይ ውጤት 3.9 አምጥቶ መመረቁ መሆኑን ይጠቅሳል።
ከተመረቀ አንድ ዓመት ሊሞላው መሆኑን የሚናገረው ታልዬ ሥራ አገኛለሁ የሚል ተስፋ ቢኖረውም የሚያመለክትባቸው ቦታዎች ሁሉ አንድም ለፈተና አለመጠራቱን ያስታውሳል።“አዲስ አበባ ውስጥ በሳምንት ከ35 ቦታዎች በላይ ያመለከትኩበት ጊዜ አለ” የሚለው ታልዬ፣ አብሯቸው ከተመረቁ ተማሪዎች መካከል የተወሰኑት ሥራ ሲያገኙ አብዛኞቹ ግን እንደእርሱ ሥራ ፈላጊ መሆናቸውን ይናገራል። ታልዬ ወደ አዲስ አበባ የመጣው የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ የቅጥር ማስታወቅያ አውጥቶ ስለነበር እንደሆነ ያስታውሳል። በተወለደበት አማራ ክልል ደግሞ የሚወጡ ማስታወቂያዎች በጣም ውስን መሆናቸውን የሚናገረው ታልዬ፣ አዲስ አበባ ግን በርካታ የሥራ ዕድሎች መኖራቸው እንደሳበው ይነገራል። ታልዬ በተመረቀበት ሙያ ሥራ ማግኘት ባለመቻሉ ከአክስቱ ልጅ ጋር ተጠግቶ ያለውን ገንዘብ በመጠቀም የጎዳና ንግድ ጀምሯል።
ሐኪሞች ሥራ የሚያጡት ለምንድን ነው?
የኦሮሚያ ሐኪሞች ማኅበር ፕሬዝዳንት እና የሕጻናት ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር በላይነህ ለታ ከሁለት ዓመት በፊት የሐኪሞች ሥራ አጥነት ከፍተኛ ችግር እንደነበር እና አሁን ግን መፍትሔ ማግኘቱን ይናገራሉ።ከሕክምና ዶክተሮች ባሻገር ግን ይላሉ ዶ/ር በላይነህ እንደ ነርስ፣ የፋርማሲ፣ የላብራቶሪ እና ሌሎች የጤና ባለሙያዎች በከፍተኛ ሁኔታ ሥራ አጥ ሆነዋል። ይህንንም በምሳሌ ሲያስረዱ በአገር ደረጃ እጥረት አለበት በሚባለው የአኔስቴዢያ (የሰመመን ባለሙያ)፣ ባለፈው ዓመት ከ500 በላይ ሞያተኞች ተመርቀው ሥራ ማጣታቸውን ማኅበሩ ገልጾ እንደነበር ይጠቅሳሉ።ሐኪሞችን የመቅጠር ሥልጣን ያላቸው ክልሎች የሚቀጥሯቸው ሐኪሞች የክልሉን የሥራ ቋንቋ የመናገር ግዴታ መጣላቸውን ተከትሎ ምናልባት ከኦሮሚያ ውጪ የሚገኙ ሌሎች ክልሎች ላይ ሐኪሞች ሥራ አጥተው ሊሆን እንደሚችልም ይናገራሉ።በኦሮሚያ ያለውን ሁኔታም ሲያስረዱ “ከሁለት ዓመት በፊት እውነት ነው ችግሩ ነበር። ይኹን እንጂ በተደጋጋሚ በተደረገ ምክክር ከሁለት ዓመት ወዲህ የሐኪሞች ሥራ አጥነት በኦሮሚያ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ተቀርፏል።” ምናልባት እንደ ችግር መጠቀስ የሚችለው ለሐኪሞች የሚሰጠው የብቃት ማረጋገጫ ፈተና በዓመት ሁለቴ፣ በየስድስት ወሩ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ተመራቂዎች ከተመረቁበት ጊዜ አንስቶ፤ ከስድስት ወር እስከ አንድ ዓመት ድረስ ያለ ሥራ መቀመጣቸው ሊሆን ይችላል። “ፈተናውን ተፈትነው ውጤታቸውን እስኪጠብቁ ድረስ፣ ከዚያም በኋላ ደግሞ ውጤታቸው ክልሎች ጋር እስኪደርስ ከስድስት ወር እስከ አንድ ዓመት ጊዜ ድረስ ሊቀመጡ ይችላሉ” ይላሉ። አክለውም “የብቃት ማረጋገጫ ፈተና ወስዶ. አልፎ፣ ፈቃድ ያገኘ ሐኪም ሳይመደብ የተቀመጠ እኛ እስከምናውቀው ድረስ አሁን የለም። ይልቁንስ በክልላችን ውስጥ ከፍተኛ የሐኪም እጥረት ነው ያለው” ይላሉ ዶ/ር በላይነህ።
በቅርብ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ለ100 ሺህ ሰው 2.5 የሕክምና ባለሙያዎች ብቻ ይዳረሳሉ። ይህ ደግሞ ከዓለም ጤና ድርጅት መስፈርት አንጻር ከታየ፣ ለ100ሺህ ሰው 10 የጤና ባለሙያዎች በሚለው እዚህ ግባ ሊባል የሚችል ቁጥር አይደለም።በሐኪሞች እጥረት ምክንያት በአንድ እና ሁለት ሐኪሞች ብቻ እየሰሩ ያሉ ትልልቅ ሆስፒታሎች መኖራቸውንም ዶ/ሩ ይገልጻሉ። በአዲስ አበባ ሥራ እየፈለገ የሚገኘው እና ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀው ዶክተር በበኩሉ፣ የደኅንነት እጦትን ጨምሮ በተለያዩ ምክንያቶች ሐኪሞች ወደ አዲስ አበባ እየፈለሱ፣ እንዲሁም ከአገር ውጪ እየሄዱ መሆኑን ጠቅሶ፣ መንግሥት ሐኪሞች ገጠር አካባቢዎችም ሄደው እንዲሰሩ ለማበረታታት የተለየ የጥቅማ ጥቅም አለማቅረቡ ምክንያት ነው ይላል።የኦሮሚያ ሐኪሞች ማኅበር ፕሬዝዳንትም እንደ አዲስ አበባ ባሉ ትልልቅ ከተሞች የመቀጠር ፍላጎት እና ራቅ ወዳሉ ቦታዎች ለመሄድ ያለመፈለግ በመኖሩ የተነሳ ሐኪሞች ሥራ የማጣት ሁኔታ ሊከሰት ይችላል። ከሁለት ዓመት በፊት የነበረውን ችግር ሲያነሱ “ሐኪም ሥራ አጥቶ ቤት እስኪቀመጥ ድረስ፣ ሰልፍ እስኪወጣ ድረስ እና ከዚያም በላይ ደርሶ ነበር። መንግሥት፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን አስተባብሮ በክልሎች የመቅጠር አቅም ፈጥሮ ችግሩ ተፈትቷል” ይላሉ። በዚህ ሂደትም አንዳንድ ክልሎች የሚፈልጉትን ያህል ሐኪም ማግኘት አለመቻላቸውን በምሳሌነት በኦሮሚያ ክልል 2 ሺህ የሚደርሱ ሐኪሞች ተፈልገው ማግኘት የተቻለው በመቶዎች የሚቆጠር ብቻ ነበር።
አገራቸውን ጥለው የሚሰደዱ ሐኪሞች
ዶ/ር በላይነህ ኢትዮጵያ ውስጥ የአንድ ተመራቂ ደመወዝ፣ ከታክስ በፊት 9ሺህ 500 ብር፣ ከአራት ዓመት ስፔሻላይዜሽን በኋላ ደግሞ 11 ሺህ ብር እንደሆነ ይገልጻሉ። ይህም ሐኪሙን ሊያኖር የሚችል በቂ ደመወዝ እንዳልሆነ በመግለጽ ሐኪሞች ወደ ጎረቤት አገራት እየተሰደዱ መሆኑን ይናገራሉ።“ይህ ደመወዝ የቤት ኪራይ እንኳ መክፈል የሚችል ስላልሆነ ሐኪሞች ቅሬታቸውን እያሰሙ ነው። ወደ ሶማሊላንድ እንኳ እየሄዱ በወር 3000 የአሜሪካ ዶላር እየተከፈላቸው ነው። ወደ ሶማሊያም እየሄዱ ነው”እዚያም 4000 የአሜሪካ ዶላር ድረስ እንደሚከፈላቸው ተናግረዋል። አክለውም አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ የሕክምና ተቋማት በሥራ ላይ ያሉ ሐኪሞች ከክፍያ ማነስ የተነሳ ፍላጎታቸው እና መነሳሳታቸው መቀነሱን ያስረዳሉ። ይህንንም ሲያስረዱ ሕዝብን ከማገልገል ስሜት ተነጥሎ የተሻለ ገቢ ወደሚገኝበት ማማተር መጀመራቸውን በአስረጅነት በመጥቀስ ነው። ይህም እንደ አንድ ባለሙያ ከፍተኛ ስጋት እንደሚፈጥርባቸው ጨምረው ገልጸዋል።በዚህ ሁሉ ፈታና ውስጥ ሆኖ የጎዳና ንግድ ላይ በመሰማራት የቀጣሪዎቹን በር የሚያንኳኳው ታልዬ ግን “ነገ ጥሩ ነገር ይኖራል፣ አዲስ ነገርም ይፈጠራል” የሚል ተስፋ አለው።
ኢትዮ ካብ ስለሚሰጠው አገልግሎት ለማወቅ ድህረገጻችንን www.ethiocab.com ይጎብኙ
የ Driver application ለማውረድ http://driver.ethiocab.com እንዲሁም የ Customer application ለማውረድ http://user.ethiocab.com
ኑ አብረን ሰርተን ትርፋችንን እንካፈል !!