የአየር ትራንስፖርት የሚሰጡ አየር መንገዶችን ማቋቋም እና በዘላቂነት በሥራ ላይ እንዲቆይ ማድረግ ከፍተኛ የገንዘብ አቅምን የሚጠይቅ የትራንስፖርት ዘርፍ ነው።

ከአውሮፕላኖች ጀምሮ አየር መንገዶችን ለማንቀሳቀስ የሚያስፈልጉ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች እንዲሁም ዋናውን ሥራ የሚሠሩትን ባለሙያዎች ለማግኘት እና ይዞ በትርፋማነት መቆየትም ከባድ ፈተና ነው።

በርካታ የአፍሪካ አገር ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ በማፍሰስ የራሳቸው የአየር መንገድ እንዲኖራቸው በተደጋጋሚ ጥረት ቢያደርጉም ኪሳራ እያጋጠማቸው ትተውታል። ያሉትም ቢሆኑ ላለመውደቅ እየተንገታገቱ ነው።

በዚህ ውስጥ ግን ጥቂት የአፍሪካ አገራት አየር መንገዶች በውድድር ውስጥ የየአገሮቻቸውን ሰንደቅ ዓላማ አንግበው አየር ላይ በመቆየት ስኬታማ ሆነዋል። ከእነዚህ ውስጥም በቀዳሚነት የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ነው።

ውድድር በበዛበት እና ከፍተኛ ወጪን በሚጠይቀው የአየር ትራንስፖርት ዘርፍ አየር መንገዶች ያላቸውን ደረጃ እና አቅም ለመለካት የተለያዩ መመዘኛዎች ይቀርባሉ።

ከእነዚህም መካከል የመዳረሻዎቻቸው ብዛት፣ የሚያጓዟቸው መንገዶኞች ቁጥር፣ ዓመታዊ ትርፍ እና የመሳሰሉት በቀዳሚነት የሚጠቀሱ ቢሆንም፤ የአየር መንገዶቹ ጡንቻ በአውሮፕላኖቻቸው ብዛት እና ዓይነትም ይለካል።

ብዛት ብቻም ሳይሆን የአውሮፕላኖች ሞዴል እና የአገልግሎት ዓይነት ከዘመናዊነታቸው ጋር ተዳምሮ የአየር መንገዶችን ግዙፍነት የሚጠቁሙ እንደሆኑ ይነገራል።

አውሮፕላኖቹ ነዳጅ ለመሙላት ሳያርፉ የሚያደርጉት የጉዞ ርዝመት፣ መንገደኞች እና ጭነት የመያዝ አቅማቸው እንዲሁም የሚገጠምላቸው ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ከብዛት በተጨማሪ የአየር መንገዶችን አቅም የሚያሳዩ ናቸው።

በዓለም ዙሪያ በአውሮፕላን ቁጥር የአሜሪካን አየር መንገዶች የሚደርስባቸው የለም። በዚህም በዓለም ከአንደኛ እስከ አራተኛ ያለውን ደረጃ ይዘው ይመራሉ።

በምድራችን በቆዳ ስፋት እና በሕዝብ ቁጥር እስያን በምትከተለው አፍሪካ የአየር ትራንስፖርት ገበያው ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኝ ዘርፍ ነው።

ይህንንም ገበያ ለመቋደስ የአህጉሪቱ አየር መንገዶች በተለይም ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ በኋላ መዳረሻዎቻቸውን ከማሳደግ ባለፈ አውሮፕላኖችን እየሸመቱ ነው።

ለዚህም የቅርብ ጊዜው ማሳያ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ነው።

አየር መንገዱ ከቦይንግ ኩባንያ ሃያ እጅግ ዘመናዊ የሆኑ 777-9 የተባሉ ሞዴል አውሮፕላኖችን ለመግዛት ከቀናት በፊት ተፈራርሟል።

ስምምነቱ ስምንት የመንገደኞች አውሮፕላኖች ግዢን እና 12 ሊፈጸም የሚችል ተጨማሪ ግዢን የሚያካትት እንደሆነ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አስታውቋል።

በ11 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ይገዛሉ የተባሉት እነዚህ አውሮፕላኖች ከቦይንግ ቤተሰብ የአውሮፕላን ሞዴሎች ጋር ሲነጻጸሩ ነዳጅን በ10 በመቶ እንደሚቆጥቡ የአየር መንገዱ ባለሥልጣናት ተናግረዋል።

5ኛ የኬንያ አየር መንገድ

የምሥራቅ አፍሪካ አየር መንገድ መፍረሱን ተከትሎ እ.አ.አ 1977 የተመሰረተው የኬንያ አየር መንገድ 44 ዓለም አቀፍ መዳረሻዎች አሉት። ከእነዚህም ውስጥ 35ቱ በአፍሪካ የሚገኙ ናቸው።

በ2020 በዓለም የጉዞ ሽልማት የአፍሪካ መሪ አየር መንገድ የተባለው የኬንያ አየር መንገድ በዓመት አራት ሚሊዮን መንገደኞችን ያጓጉዛል።

የአየር መንገዱ 48.9 በመቶው የባለቤትነት ድርሻ የኬኒያ መንግሥት የሆነው አየር መንገዱ የተለያየ ዓይነት ያላቸው 32 አውሮፕላኖች አሉት። እሱም

4ኛ ሮያል ኤር ሞሮኮ

በሞሮኮ ሰንደቅ ዓላማ ስር የሚበረው ሮያል ኤር ሞሮኮ እ.አ.አ በ1957 ነው የተመሠረተው። በአብላጫው በሞሮኮ መንግሥት ባለቤትነት የተያዘም ሲሆን፤ በካዛብላንካ መሐመድ አራተኛ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ማዕከሉን አድርጎ ይበራል።

በአብዛኛው ጉዞውን በአገር ውስጥ እና በቀጣናው አገራት ያደረገው አየር መንገዱ 89 መዳረሻዎች ሲኖሩት፣ ለእነዚህ ጉዞዎቹም ድብልቅ የአውሮፕላን ዓይነቶችን ይጠቀማል። በአጠቃላይ 51 አውሮፕላኖች አሉት።

3ኛ ኤር አልጄሪያ

እ.አ.አ በ1946 አልጄሪያ የፈረንሳይ ቅኝ ግዛት አካል እያለች የተመሠረተው ኤር አልጄሪያ ወደ አውሮፓ መንገዶኞችን ለማጓጓዝ የተመሠረተ ነው።

አልጄሪያ በ1962 ነጻነቷን ስታገኝ በመንግሥት ቁጥጥር ስር የገባው አየር መንገዱ፣ በ28 አገራት 78 የአገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ መዳረሻዎች አሉት።

አየር መንገዱ በቅርቡም ኢትዮጵያን አዲስ መዳረሻው በማድረግ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።

ኤር አልጄሪያ ሰፋ ያሉ ቅርጽ ያላቸውን የአውሮፕላን ሞዴሎች በመጠቀም የሚታወቅ ሲሆን፣ በአጠቃላይ የ55 አውሮፕላኖች ባለቤት ነው።

2ኛ ኢጅብት ኤር

እ.አ.አ በ1932 በመመሥረት ከዓለም ቀደምት አየር መንገዶች ተርታ የሚመደበው የግብፁ አየር መንገድ ኢጅብት ኤር፤ እዚያው በአገር ውስጥ ከካይሮ ወደ አሌክሳንዲሪያ በመብረር ነበር አገልግሎት የጀመረው።

በአገሪቱ መንግሥት ባለቤትነት የሚተዳደረው አየር መንግዱ፤ 100 ዓለም አቀፍ መዳረሻዎች አሉት። የግብፅ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያን ዋነኛ ማዕከሉ አድርጎም ይበራል።

በአፍሪካ ግዙፍ የአየር የጭነት አገልግሎት (ካርጎ) የሚሰጠው አየር መንገዱ፤ በመጪዎቹ ዓመታት የአውሮፕላኖቹን ቁጥር እንደሚያሳድግ ይጠበቃል።

የኤርባስ እና የቦይንግ አውሮፕላኖችን በአብዛኛው የያዘው ኢጅብት ኤር፤ 82 አውሮፕላኖች አሉት።

1ኛ የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ከስምንት አስርት ዓመታት በፊት በአጼ ኃይለ ሥላሴ የተመሠረተው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በፈጣን እድገቱ በአፍሪካ ስመ ጥር ነው።

አፍሪካን ከዓለም፤ ዓለምን ከአፍሪካ በማስተሳሰርም ስሙን ገንብቷል።

ዋና መናኸሪያውን አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ላይ አድርጎ፤ በቶጎ ሎሜ፣ በማላዊ ሊሎንፍዌ፣ በዛምቢያ ሉሳካ ተጨማሪ መናኸሪያዎችን ከፍቷል።

የአፍሪካን መንገደኞች እና ጭነቶችን በማጓጓዝ ከአህጉሪቱ የአየር ትራንስፖርት ገበያ የአንበሳውን ድርሻ የሚይዘው አየር መንገዱ፤ ዘመናዊ በሆኑ አውሮፕላኖች በአምስት አህጉራት ከ150 በላይ ወደ ሆኑ መዳረሻዎቹ ይበራል።

የቦይንግ፣ የኤርባስ እና የቦምባርድኤር ምርት የሆኑ የተለያዩ አውሮፕላኖች ያሉት የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአጠቃላይ 148 አውሮፕላኖችን በአየር ላይ በማሰማራት በአፍሪካ ውስጥ ተፎካካሪ የሌለው ለመሆን ችሏል።

አየር መንገዱ ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያ መንግሥት ባለቤትነት ስር የሚተዳደር ሲሆን፣ በየዓመቱ በቢሊዮኖች ዶላር የሚቆጠር የውጭ ምንዛሪን ለአገሪቱ ያስገኛል።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ ፡-BBC NEWS

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *