በየዓመቱ ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን በተመለከተ ከመገናኛ ብዙሃን ወይም በዙሪያዎ ካሉ ሰዎች ሰምተው ይሆናል።

ነገር ግን ይህች ዕለት ለምን እንደምትከበር? መቼ እንደምትከበር? ዕለቷስ ክብረ በዓል ወይስ የአመፅ ቀን ? በተመሳሳይስ ዓለም አቀፍ የወንዶች ቀን አለ? በዚህ ዓመትስ ምን አይነት ዝግቶች ይኖራሉ?

ለአስርት ዓመታት ያህል በዓለማችን የሚገኙ ሕዝቦች ማርች 8ን ለሴቶች ለየት ያለች ቀን እንደሆነች አድርገው ይመለከቷታል። ለምን?

እንዴት ተጀመረ?

የዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ታሪካዊ መነሻዋን ያደረገችው የሠራተኞች አንቅስቃሴን ሲሆን በአሁኑ ወቅት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዕውቅና የተሰጣት ዓመታዊ በዓል ለመሆን በቅታለች።

የክብረ በዓሏ ጅማሮ በአውሮፓውያኑ 1908 ነው። በወቅቱ 15 ሺህ የሚሆኑ ሴቶች በኒውዮርክ ከተማ ላይ የሥራ ሰዓት መሻሻል (ማጠር)፣ የተሻለ ክፍያና ሴቶች በምርጫ መሳተፍ አለባቸው በሚል የተቃውሞ ሰልፍ አካሄዱ።

ከአንድ ዓመት በኋላም የአሜሪካ ሶሻሊስት ፓርቱ የመጀመሪያዋን ብሔራዊ የሴቶች ቀን አወጀ።

ቀኗን ዓለም አቀፍ የማድረግ ሃሳቡ የመጣው ክላራ ዜትኪን በምትባል ግለሰብ አማካኝነት ነው።

በዴንማርኳ ኮፐንሃገን በአውሮፓውያኑ 1910 የሴት ሠራተኞች ዓለም አቀፍ ጉባኤ ላይ ነበር ሃሳቡን ያነሳችው።

በወቅቱ ከ17 አገራት የተውጣጡ 100 ሴቶች ተሳትፈውበት የነበረ ሲሆን በሃሳቧም ሙሉ በሙሉ ነው የተስማሙት።

ለመጀመሪያ ጊዜም በኦስትሪያ፣ ዴንማርክ፣ ጀርመንና ስዊዘርላንድ በአውሮፓውያኑ 1911 ተከበረች።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ይፋዊ ሆና መከበር የጀመረችው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ክብረ በዓሏን ማክበር በጀመረባት በአውሮፓውያኑ 1975 ነው።

ለመጀመሪያ ጊዜ “የኋላውን ማክበር፤ የወደፊቱን ማቀድ” በሚል በተባበሩት መንግሥታት ባወጣው መሪ ቃል በ1996 ነበረ በዓለም አቀፍ ደረጃ በደመቀ ሁኔታ የተከበረችው።

ዓለም አቀፏ የሴቶች ቀን የምትዘክረው ሴቶች በማኅረበሰቡ የደረሰባቸውን ጭቆናን ተቋቁመው በፖለቲካውና በምጣኔ ሀብቱ ያገኙትን ትሩፋት ትዘክራለች።

ክብረ በዓሏ መሰረቷ ፓለቲካዊ ዓመፅ ሲሆን በአሁንም ወቅት በዓለም ላይ የሰፈነውን የተዛባ የሥርዓተ-ፆታ ኃይል ሚዛንን ለማስተካከል በተለያዩ ሰልፎችና የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ትዘከራለች።

መቼ ትከበራለች?

በየዓመቱ ማርች 8 ወይም በዘንድሮው በኢትዮጵያ አቆጣጠር የካቲት 29/2013 ዓ.ም ትከበራለች። ክላራ በዓሏ በዓለም አቀፍነት ደረጃ እንድትከበር ሃሳብ ስታመነጭ የቆረጠችው ቀን አልነበረም።

በመጀመሪያው የዓለም ጦርነት አካባቢ የሩሲያ ሴቶች “ዳቦና ሰላም” በሚል ሰልፍ አደረጉ። በወቅቱ የነበረው ንጉሣዊ ሥርዓት ስልጣን የለቀቀ ሲሆን ጊዜያዊ አስተዳዳሪውም ሴቶች በምርጫ እንዲሳተፉ ፈቀደ።

እነዚህ ሴቶች ተቃውሞ ያነሱባት ቀን በጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር ማርች (መጋቢት) 8 ዕለት ናት።

ቀኗ ለምን ታስፈልገናለች?

“በሚቀጥለው ክፍለ ዘመን እንኳን የሥርዓተ-ፆታ ኃይል መዛባትን ማስተካከል አንችልም” ያሉት የዓለም አቀፍ ሴቶች ቀን ዘመቻ አንቀሳቃሽ ሲሆኑ፣ ይህንንም ያሉት ዓለም አቀፉ የኢኮኖሚክ ፎረምን በመጥቀስ ነው።

“እዚህ ያለነው ሁላችንም አይደለም መጪዎቹ ልጆቻችን ኢ-ፍትሃዊ የሆነው የሥርዓተ-ፆታ ተስተካክሎ ሊያዩት አይችሉም” ብለዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በቅርቡ የተባበሩት መንግሥታት የሴቶች ተቋም (ዩኤን ውሜን) ባወጣው መረጃ መሠረት የኮሮናቫይረስ ወረረሽኝ ሥርዓተ-ፆታ ላይ የተሠሩትን ሥራዎች ወደ ኋላ 25 ዓመታት የሚጎትት ነው ብለውታል።

በተጨማሪም ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የተከሰቱት ግጭቶች እና ጦርነቶች በሴቶች ደኅንነት ላይ ካስከተሏቸው ስጋቶች ባሻገር ምጣኔ ሀብታዊ መናጋትን ፈጥረዋል።

በዩክሬን እና በሩሲያ እንዲሁም በእስራኤል እና ሐማስ መካከል የሚካሄዱት ጦርነቶች በሴቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳትን አድርሰዋል።

በተጨማሪም እነዚህ ጦርነቶች ባስከተሏቸው የምርት እና የአቅርቦቶች መስተጓጎል ምክንያት በመሠረታዊ ምርቶች እና አገለግሎቶች ላይ መቋረጥን በመፍጠራቸው በመላው ዓለም ከፍተኛ ምጣኔ ሃብታዊ ጫናን ፈጥረዋል።

ይህ ደግሞ የዋጋ መናርን በማስከተል በተለይ በማደግ ላይ ባሉ አገራት ውስጥ በሚገኙ ሴቶች ኑሮ እና ሕይወት ላይ ጫናን ፈጥሯል።

ጦርነቶች እና የኑሮ ውድነት ልጆች የማሳደግ እና ቤተሰብ የመንከባከብ ኃላፊነትን በዋናነት በሚወጡት ሴቶች ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ስላላቸው። በሥራም ይሁን በትምህርት ሊያገኙዋቸው የሚችሉ ዕድሎች ላይ መደናቀፍን ይፈጥራሉ።

የዘንድሮው የዓለም ሴቶች ቀን መሪ ቃል ምንድን ነው?

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዚህ ዓመት (2024 እአአ) የሴቶች ቀን መሪ ቃል “የሴቶችን እድገት ለማፋጠን ማዋዕለ ነዋይ ማፍሰስ” የሚል ሲሆን፣ ትኩረቱን ለፆታ እኩልነት የሚወሰዱ እርምጃዎች ላይ ያደረገ ነው።

“ግጭቶች እና የዋጋ ውድነት ከዓለማችን 75 በመቶ የሚሆኑ አገራትን ለሕዝባዊ አግልግሎት የሚያወጡትን ገንዘብ እንዲቀንሱ ሊያደርጓቸው ይችላል፤ ይህ ደግሞ የሴቶችን መሠረታዊ ግልጋሎቶች ያስተጓጉለዋል” ሲል የተባበሩት መንግሥታት አስጠንቅቋል።

የዓለም አቀፉ የሴቶች ቀን ድረ ገጽ ደግሞ “አካታችንነትን እናጎልበት” የሚለውን መሪ ቃል ለዚህ ዓመት መርጧል። የበዓሉ አዘጋጆች “መሰናክሎችን እናስወገድ፣ የተሳሳቱ አመለካከቶችን እንዋጋ፣ ሴቶች ተቀባይነት የሚያገኙበት እና የሚከበሩበትን ሁኔታ እንፍጠር” ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል። “ ”

ዓለም አቀፍ የወንዶች ቀን የሚባል አለ?

አዎ አለ! ቀኑም የሚከበረው ኖቬምበር (ኅዳር) 19 ነው።

ዕለቱ መከበር የጀመረው ከአውሮፓውያኑ 1990ዎቹ በኋላ ቢሆንም ግን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዕውቅና የለውም።

በዓለም ላይ ዩናይትድ ኪንግደምን ጨምሮ በ80 አገራት ይከበራል።

ዕለቱም ወንዶች በዓለም ላይ ያመጧቸውን አዎንታዊ እሴቶች፣ ለቤተሰባቸውና ለማኅበረሰቡ እያደረጉት ያለውን አስተዋፅኦ ይዘክራል።

ከዚህም በተጨማሪ አርዓያ የሚሆኑ ወንዶችን ማሳየትና በወንዶች ጤንነት ላይም ግንዛቤ ለመፍጠር ያለመ ነው።

ባለፈው ዓመትም “የተሻለ ጤና ለወንዶች ” በሚል መሪ ቃል ተከብሯል።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ ፡-BBC

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *