![](https://ethiocab.com/wp-content/uploads/2023/09/55a2af00-591e-11ee-83bb-5f9bffc8f569.jpg.webp)
22 መስከረም 2023
የልዑል አለማየሁ የፀጉር ዘለላና፣ ከመቅደላ ተዘርፎ የተወሰደ ታቦት እና የተለያዩ የኢትዮጵያ ቅርሶች ለኢትዮጵያ ተመላሽ ተደረጉ። በለንደን የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ የልዑል አለማየሁ የፀጉር ዘለላ እና ከመቅደላ ጦርነት በኋላ በእንግሊዝ ጦር ተዘርፈው የተወሰዱ ቅርሶች መረከቡን ባወጠው መግለጫ አስታውቋል። ኤምባሲው ከተረከባቸው ቁሶች መካከል ከመቅደላ የተዘረፈ የመድሃኒያለም ታቦት፣ የልዑል አለማየሁ የፀጉር ዘለላ፣ ከብር የተሰሩና በነሃስ የተለበጡ ሦስት ዋንጫዎች እንዲሁም በዘመኑ ጦርነት ላይ የዋለ የጦር ጋሻ ይገኙበታል። ትናንት ሐሙስ መስከረም 10/2016 ዓ.ም. በለንደን ከተማ በተካሄደው የቅርሶቹ ርክክብ ሥነ–ስርዓት ላይ በዩናይትድ ኪንግደም የኢትዮጵያ ኤምባሲ አመራሮች፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እና የብሔራዊ ቅርስ አስመላሽ ኮሚቴ ተወካዮች እና ቅርሶቹን ለማሰመለስ የተባበሩ አካላት ተገኝተዋል። በርክክብ ሥነ–ስርዓቱ ላይ በዩኬ የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈሪ መለሰ ኤምባሲያቸው ከመቅደላና ከሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች ተዘርፈው ወደ ዩናይትድ ኪንግደም የተጋዙ ቅርሶች ለማስመለስ ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት፣ ለሙዚየም የሥራ ኃላፊዎች፣ ለጥናትና ምርምር ተቋማት፣ ለቅርስ አስመላሽ እና ተሟጋቾች በተደጋጋሚ ጥያቄ ማቅረቡን አስታውሰው፣ይህ ጥረት ይቀጥላል ስለማለታቸው ኤምባሲው አስታውቋል። አምባሳደር ተፈሪ መለሰ ኤምባሲው ትናንት ሐሙስ የተረከባቸው ቅርሶች በተገቢው ቦታቸው እንዲቀመጡ ለማድረግ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚላኩ ተናግረዋል።
በእአአ 1868 ከመቅደላ ጦርነት በኋላ በእንግሊዝ ጦር ተዘርፈው ከተወሰዱት መካከል የመድሃኒያለም ታቦት አንዱ ሲሆን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ታቦቱን እንዲረከበው መደረጉ ተገልጿል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ልዑክን የመሩት መጋቢ ሀዲስ ቀሲስ አባተ ጎበና ታቦቱ እንዲመለስ መደረጉ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ላቅ ያለ ሃይማኖታዊ ፋይዳ ያለው መሆኑን ገልጸው፤ ታቦቱ በተገቢው የሃይማኖት ሥርአት ተይዞ በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚላክ ገልጸዋል።
![](https://ethiocab.com/wp-content/uploads/2023/09/4c6de6c0-590a-11ee-b05e-1b7eb1786286.jpg.webp)
የልዑል አለማየሁ የፀጉር ዘለላ
የልዑል አለማየሁ የፀጉር ዘለላ ወደ ኢትዮጵያ ይመለሳል መባሉ የአጼ ቴዎድሮስ ቤተሰብ እንዳስደስተ የዳግማዊ ቴዎድሮስ 4ኛ ትውልድ ቤተሰብ የሆነው ፋሲል ሚናስ ለቢቢሲ ገልጿል። ፋሲል የልዑሉ የፀጉር ዘለላ መመለስ “እንደ አንድ ኢትዮጵያዊና ቤተሰብነቴ እጅግ የላቀ ደስታና ትርጉም አለው” ያለ ሲሆን በቀጣይ “የልዑል አለማየሁ ቅሪት አፅም መመለስ ቢችል መልካም ነው እላለሁ” ብሏል። ፋሲል ይህን ይበል እንጂ ባኪንግሃም ቤተ መንግሥት በዊንድሶር ካስል ውስጥ በ19ኛው ክፍለ ዘመን የተቀበረውን የኢትዮጵያዊ ልዑል አለማየሁ ቴዎድሮስን አፅም እንዲመለስ የቀረበለትን ጥያቄ እንደማይቀበል መግለጹ ይታወሳል። ቤተሰብ፣ የልዑሉ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ እና መንግሥት የልዑሉ አፅም ወደ ትውልድ አገሩ እንዲመለስ ቢጠይቁም የእንግሊዝ ንጉሥውያን ቤተሰብ ግን “ለጥያቄው ምላሽ መስጠት አይቻለንም” ማለታቸው ይታወሳል። አንትሮፖሎጂስት እና የተዘረፉ የኢትዮጵያ ቅርሶች አስመላሽ ኮሚቴ አባል የሆኑት አሉላ ፓንክረስት ቅርሶቹ እንዲመለሱ መደረጉ አዎንታዊ እርምጃ መሆኑን ገልጸው እርምጃው በእንግሊዝ እና በኢትዮጵያ ተቋማት፣ ሙዚየሞች፣ ተመራማሪዎች መካከል የተሻለ ግንኙነት እና ትብብር ለመፍጠር ጥሩ መንገድንም ይፈጥራል ብለዋል። ትናንት የኢትዮጵያ ኤምባሲ እንዲረከባቸው የተደረጉ ቅርሶች ተመላሽ እንዲሆኑ ከፍተኛ ትብብር ሲያደርግ ነበር የተባለው ሼሄራዜድ በጎ አድራጎት ድርጅት የቅርሶቹ መመለስን በተመለከተ ባወጣው መግለጫ፣ የልዑል አለማየሁ የፀጉር ዘለላ ከካፒኔ ስፒዲ ቤተሰብ አባላት የተገኘ መሆኑን ገልጿል። ልዑሉ ከመቅደላ ይዘውት የወጡት ካፒቴን ስፒዲ የተባሉ የእንግሊዝ ጦር መኮንን ሲሆኑ ልዑሉ በለጋ ዕድሜው እንግሊዝ ከደረሰ በኋላም ከዚሁ የጦር መኮንን ጋር አብሮ መኖር ጀምሮ ነበር። ኢትዮ ካብ ይሄን አስደሳች ዜና በመስማታችን የተሰማንን ደስታ እንገልፃለን !! በህብረት ሰርተን ትርፋችንን እናካፍሎት የሚለው ኢትዮ ካብ ነው !!
አብራችሁን በአጋርነት ለመስራት ድህረገጻችንን www.ethiocab.com ይጎብኙ
የ Driver application ለማውረድ http://driver.ethiocab.com እንዲሁም የ Customer application ለማውረድ http://user.ethiocab.com
ኑ አብረን ሰርተን ትርፋችንን እንካፈል !!