![](https://ethiocab.com/wp-content/uploads/2023/10/494bb580-72f0-11ee-8771-77c95a2dcbae.jpg.webp)
25 ጥቅምት 2023
ይህ የሆነው ከሃያ አምስት ዓመታት በፊት ነው – በ1991 ዓ.ም.።የቤተሰብ ጋራዥ አስተዳዳሪ የነበሩት ወይዘሮ የወርቅውሃ ተከስተ ያኔ እድሜያቸው 42 አካባቢ ነበረ። አባታቸው በመታመማቸው ብዙ ጊዜያቸውን ሆስፒታል ውስጥ ያሳልፉ እንደነበር ያስታውሳሉ። እናም አንድ ቀን ከአባታቸው ጎን ተቀምጠው ሳለ የግራ ጡታቸው አካባቢ ለደቂቃ ያህል የቆየ ሕመም ተሰማቸው። ደንግጠው ጡታቸውን ነካኩ – የሆነ ጠጠር ያለ ነገር አለ። በቀጣዩ ቀን ጋዜጣ ሲያነቡ ያጋጠማቸው የጡት ምርመራን የተመለከተ የሆስፒታል ማስታወቂያ፣ ከአንድ ቀን በፊት የተሰማቸውን ሕመም አስታወሳቸው። በተቻሉት መጠን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በማድረግ እና ጤናማ የአመጋገብ ሥርዓትን በመከተል ጤናማ ሕይወት ለመምራት ይጥራሉ። በአጠቃላይ ግን በጤና ጉዳይ ላይ አይዘናጉም። እናም በነጋታው ማስታወቂያውን ወዳዩት ሆስፒታል ሄደው ተመረመሩ። ሐኪም በጡታቸው ውስጥ የሚታይ ነገር እንዳለ እንዳለ እና ተጨማሪ ምርመራ ለማድረግ “ከጡቴ ላይ የሆነ ነገር” ተወሰደ ይላሉ። ወይዘሮ የወርቅውሃ በወቅቱ ስለጡት ካንሰር የሚያውቁት ነገር አልነበረም። የባዮፕሲ – ከጡታቸው የሕብረዋስ ናሙና ተወስዶ ምርመራ ከተደረገ በኋላ፣ በውጤቱ በፍጥነት ሊስፋፋ የሚችል የካንሰር ሕዋስ መገኘቱን እና ሕክምና ማድረግ አስፈላጊ መሆኑ ተነገራቸው።
እውነታን መጋፈጥ
ወይዘሮ የወርቅውሃ “ምንድነው የሚደረገው?” ብለው ጠየቁ። አደገኛውን ዕጢ የያዘውን ጡታቸውን በቀዶ ሕክምና በማስወገድ ካንሰሩ እንዳይሰራጭ ከተደረገ እና መድኃኒት ከወሰዱ ሊድኑ እንደሚችሉ ተነገራቸው። ይህንኑ የሐኪሞቹን የመፍትሄ ምክር ለባለቤታቸው በነገሯቸው ጊዜ በጣም እንደደነገጡ እና “በአስቸኳይ” አሜሪካ ወደ ልጆቻቸው ጋር በመሄድ መታከም እንዳለባቸው ሃሳብ ቢያርቡም እሳቸው ፈቃደኛ አልሆኑም። ወይዘሮ የወርቅውሃ በሁኔታው “ከእኔ በላይ የደነገጠው ባሌ ነው። እኔ በጣም ተረጋግቼ ነበር፤ ምክንያቱም ወዲያው ነው የተቀበልኩት። ለችግሩ መፍትሄ ካለው በመረበሽ የሚመጣ ነገር የለም” ይላሉ። ሰዎች ካንሰር እንዳለባቸው አምነው ከተቀበሉ ብዙ ጊዜ የተስፋ ስሜት እንደሚፈጥርባቸው የሥነ አእምሮ ሐኪሞች ይናገራሉ። ሐዘን እና ብስጭት ግን የምግብ ፍላጎታቸውን በመቀነስ ሊያዳክማቸው እና ሕክምናቸውን በንቃት እንዳይከታተሉ ሊያደርጋቸው ይችላል። ወይዘሮ የወርቅውሃም ሕመማቸውን ተቀብለው የተለየ ተጽእኖ ሳይፈጥርባቸው የዕለት ከዕለት ኑሯቸው ቀጠሉ። ለሕክምናው በሚዘጋጁበት ወቅትም ጎን ለጎን የተለመደ ሥራቸውን ያከናውኑ ነበር። ቤተሰባቸውን አረጋግተው በቀጠሯቸው መሠረት ብቻቸውን ወደ ሆስፒታል መሄዳቸውን የሚናገሩት ወ/ሮ ወርቅውሃ፣ በቀዶ ሕክምና የግራ ጡታቸው ከተወገደ በኋላ ለሁለት ቀን እዚያው ቆይተዋል። በሦስተኛው ቀን ግን ራሳቸው መኪናቸውን እያሽከረከሩ ከሆስፒታል ወጥተው ወደ ቤታቸው ተመለሱ።
የካንሰር ሕክምና እና የዕለት ከዕለት ሕይወት
ቀጣዩ ሕክምና ኬሞቴራፒ ነበር። ኬሞቴራፒ ኃይለኛ ኬሚካሎችን በመጠቀም በሰውነት ውስጥ በፍጥነት በመሰራጨት ላይ ያሉ የካንሰር ሕዋሳትን ለማጥፋት የሚደረግ ሕክምና ነው። በአብዛኛውም ካንሰርን ለማከም ይውላል። “በጣም ከባድ ነበር” ይላሉ የኬሞቴራፒ ሕክምናውን ሲያስታውሱ። የመጀመሪያው ቀን ሕክምና አደከማቸው። ጨጓራቸውንም በጣም ታመው ነበር።”ኬሞቴራፒ አካላዊ እና ስሜታዊ ለውጥን ሊያስከትል ስለሚችል እረፍት እንደሚያስፈልግ ባለሙያዎች ይመክራሉ። ይሁን እንጂ አንዳንድ ታካሚዎች መደበኛ ሕይወታቸውን መምራት እንደሚችሉ እና ሕክምና ወደ ሥራቸው የሚገቡም እንዳሉ ይናገራሉ። ይህም የታካሚዎች ትኩረት ሥራ ላይ እንዲሆን እና እንዳይጨነቁ ሊያግዛቸው ይችላል። ይሄ ለወይዘሮ የወርቅውሃ እውነት ነበር።“ሥራ ከሕመሙ እና ከሁሉም ነገር መደበቂያዬ ነበር። ከሕክምናው በኋላ ወደ ሥራ ስገባ ምንም ነገር አላስታውስም። እሰራለሁ፣ ይደክመኛል፣ እተኛለሁ በቃ።”የኬሞቴራፒ ሕክምና የጎንዮሽ ጉዳት አለው። “አካላዊ ለውጥ እንደሚኖር ሐኪሙ ነግሮኝ ነበር” ይላሉ። ለምሳሌም ፀጉራቸው ሊረግፍ እንደሚችል አስጠንቅቋቸው ነበር። እሳቸውም “ምን ችግር አለው? ጡቴስ ተቆርጦ የለም ወይ? አልኩት” ይላሉ። ነገር ግን እንደ አጋጣሚ ሆኖ ደግሞ አንዲትም ፀጉር እንዳልረገፈባቸው ነው የሚናገሩት። ይሁን እንጂ ምግብ እንደፈለጉ መመገብ ስላልቻሉ መጀመሪያ ላይ ከስተው እንደነበር ያስታውሳሉ።“ከዚያ ውጪ ምንም አልሆንኩም።”
በሕክምና ወቅት እና ከሕክምና በኋላም በአኗኗራቸው ላይ የመጣ ለውጥ እንዳልነበረ የሚናገሩት ወይዘሮ የወርቅውሃ፣ የኬሞቴራፒ ሕክምና እንደጨረሱ ወዲያውኑ ወደ ጂም ተመለሰው የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የማድረግ ልምዳቸውን ቀጥለዋል። በተጨማሪም በወሲባዊ ሕይወታቸው ላይ “ምንም ዓይነት ለውጥ አልነበረም። ምንም! ሁሉም ነገር እንደድሮው ነበር” ይላሉ። የካንሰር ታካሚዎች በተለየ ሊከተሉት የሚገባ የአመጋገብ ሥርዓት እንደሌለ እና እንዲመገቡ ወይም እንዳይመገቡ የተነገራቸው ምግብ እንደሌለ በመግለጽ፣ ይሁን እንጂ ለአጠቃላይ ጤንነት “አንድ ሰው አመጋገቡን ቢያስተካል ይመረጣል” ሲሉ ይመክራሉ። የጤና ባለሙያዎችም ጤናማ የአኗኗር ዘይቤን ይመክራሉ፤ ጤናማ አመጋገብ መከተል፣ ቋሚ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ማድረግ እና በቂ እረፍት ማግኘት የካንሰር ሕመም እና ሕክምናው ሊያስከትለው የሚችለውን ውጥረት እና ድካም ለመቆጣጠር እንደሚያግዝ ያስረዳሉ። የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ሰዎች የጎንዮሽ ጉዳቶችን በተሻለ ሁኔታ መቋቋም ብቻ ሳይሆን፣ ረዘም ላለ ጊዜ ሊኖሩ እንደሚችሉ ጥናቶት ያመለክታሉ።
ለማን ይነገራል?
የካንሰር ታማሚዎች እና ታካሚዎች ሁኔታቸውን በተመለከተ ለማን መናገር እንዳለባቸው የሚወስኑት ራሳቸው ናቸው። ዝግጁ እስካልሆኑ ድረስ ደግሞ አለመናገር ይችላሉ። ወይዘሮ የወርቅውሃ ካንሰር እንደታመሙ ያውቁ የነበሩ ጥቂት ሰዎች ብቻ ናቸው – መጀመሪያ ባለቤታቸው በኋላም ልጆቻቸው።“እናቴ፣ አባቴ፣ እህቴ እና ወንድሜ አያውቁም ነበር” በማለት ለብዙ ሰው አለመናገራቸው እንደጠቀማቸው ያስረዳሉ። ለሁሉም ሰው ተናግረው ቢሆን ኖሮ “መንገዴ ላይ መቆማቸው አይቀርም። ይህንን ሞክሪ፣ ያንን አድርጊ፣ ያኛው ይሻላል የሚለው መካሪ ይበዛና መያዣ መጨበጫ ሊጠፋል” ይላሉ። ይህም ውሳኔያቸው ትኩረት አድርገው ሕክምናቸውን በአግባቡ ለመከታተል እንደረዳቸው በመጥቀስ፣ ሌሎችም ባህላዊ ሕክምናን የመሳሰሉ ነገሮችን በመሞከር ጊዜያቸውን እንዳያባክኑ ይመክራሉ። ወይዘሮ የወርቅውሃ ከሕክምናቸው በኋላ ስላለፉበት ሁኔታ ከሌሎች ጋር መወያየት እና መመካከር እንዲሁም ስለሁኔታቸው ልምድ መለዋወጥ ጀመሩ። በዚህ ሂደትም በተመሳሳይ የጤና ችግር ውስጥ ሆነው የተጨነቁ ሰዎችን ከሌሎች ጎደኞቻቸው ጋር በመሆን ለመምከር እና ለመርዳት የራቸውን ጥረት ማድረግ ጀመሩ። ካንሰር ካለባቸው ወይ ከካንሰር ከዳኑ ሰዎች ጋር መነጋገር ስለበሽታው እና ስለሕክምናው የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖር እንደሚያስችል ባለሙያዎች ይገልጻሉ። ይህም በሽታውን እና ሕክምናውን በተሻለ ለመቋቋም እና ለመከታተል ይረዳል። የካንሰር ተጠቂዎችን ማሰባሰብ ከባድ ነበር የሚሉት ወይዘሮ የወርቅውሃ እራሳቸው ፈቃደኛ ሆነው በየሆስፒታሉ እየተዘዋወሩ እንዲሰባሰቡ ጥረት አደረጉ። ይሁን እንጂ ሕመሙ “እንዲታወቅባቸው የማይፈልጉ ብዙ ሰዎች አሉ” በማለት ብዙ ታካሚዎች ፈቃደኛ ባለመሆናቸው አንዳንድ ጊዜ እነሱን ለማሳመን ልብሳቸውን አውልቀው በቀዶ ሕክምና የተወገደውን ጡታቸውን ለማሳየት ይገደዱ እንደነበር ያስታውሳሉ። በዚህም የኢትዮጵያ ካንሰር ሕሙማን ማኅበር እንዲጠነሰስ ያስቻለ የመሰረት ድንጋይ ነበር።
ለሌሎች መትረፍ
ወይዘሮ የወርቅውሃ ከሌሎች ጓደኞቻቸው ጋር የጀመሩት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ቀላል አልነበረም። የካንሰር ታካሚዎችን ከማሰባሰብ እና ልምድ ከማካፈል ባለፈ ሰዎቹን መንከባከብ፣ መመገብ፣ ልብሳቸውን ማውለቅና ገላቸውን ማጠብ ያካተተ ተግባር ነበር። በዚያን ወቅት እንዲህ ዓይነት አገልግሎት መስጠታቸው “ሕዝቡን ማገዝ” የሚል አስተሳሰብ እንዲሰርጽባቸው እንዳደረገ ወይዘሮ የወርቅውሃ ይናገራሉ። ኋላ ላይም የመጀመርያ ልጃቸው ከዚህ ዓለም ሲለይ፣ ልጆቹን ለማሳደግ ወደ አሜሪካ ሲሄዱ ይህ ሕዝብን ማገዝ ወይ ማገልገል የሚለው ፍላጎታቸው እያየለ መጣ። እዚያም የነርስነት ሙያን ተምረው ቋሚ ሥራቸው አደረጉት። ወይዘሮ የወርቅውሃ እነሆ የጡት ካንሰር ተገኝቶባቸው ሕክምና ተከታትለው ከዳኑ ሃያ አምስት ዓመት ሊሞላቸው ነው።“አንድ ነገር ከመጣ መፍትሔ መፈለግ ነው እንጂ፣ ወደዚያ ወደዚህ ማለት ለበሽታው ጊዜ መስጠት ነው። ካንሰር በጊዜ ታውቆ በጊዜ ከታከመ ይዳናል። እኔም ለዚህ ምስክር ነኝ ” ይላሉ።
ኢትዮ ካብ ስለሚሰጠው አገልግሎት ለማወቅ ድህረገጻችንን www.ethiocab.com ይጎብኙ
የ Driver application ለማውረድ http://driver.ethiocab.com እንዲሁም የ Customer application ለማውረድ http://user.ethiocab.com
ኑ አብረን ሰርተን ትርፋችንን እንካፈል !!