19 መስከረም 2023
ይህ የሆነው ሐዋሳ ከተማ ነው። በሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ ጨዋታ ወላይታ ዲቻ ከኡጋንዳው ኪይንዳ ቦይስ ሲጫወቱ።ከእረፍት መልስ የኪይንዳ ቦይስ ተጫዋቹ ካልውሌ ፍራንክ ከዲቻው አስናቀ አምታታው ጋር ተጋጭቶ ይወድቃል። ተጫዋቹ ምላሱን መዋጡን የተረዱ የሕክምና ባለሙያዎች ከተቀመጡበት ተነስተው እየሮጡ ወደሜዳ ይገባሉ። ነፍስ ግቢ ነፍስ ውጪ። የሕክምና ባለሙያው ብሩክ ደበበ ሁለት ጣቶቹን ከትቶ ከተጫዋቹ ጥርሶች ጋር እየታገለ ሕይወት አትርፏል። የተፈጠረውን በዝርዝር እንዲያስረዳን የጠየቅነው ብሩክ “ሕይወት ከሚጠፋ የእኔ እጅግ ቢቆረጥ ይሻላል” ብየ ገባሁ ይላል። ጎፈሬ ዋንጫ የሲዳማ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጎፈሬ ከተሰኘው የስፖርት ትጥቅ አምራች ጋር በትብብር የሚያዘጋጁት ነው። በዚህ ውድድር በተጋባዥነት የመጣው የኡጋንዳው ኪይንዳ ቦይስ ከወላይታ ዲቻ ተጋጥሞ 3-2 ተሸንፏል። ነገር ግን ከጨዋታው ውጤት በላይ እጅግ አነጋጋሪ የነበረው ጉዳይ በሁለተኛው አጋማሽ የሆነው ነው።“እኔ የሲዳማ ቡና ፊዚዮ ቴራፒስት ነኝ። ጨዋታውን ‘ትሪቡን’ ላይ ሆነን እየተከታተልን ነበር። በሁለተኛው አጋማሽ የኡጋንዳው ቡድን ተጫዋች ምላሱን ዋጠ። ከዚያ ተሯሩጠን ገባን” ይላል ብሩክ።“ምላስ ማውጫ መሣሪያ [ኪት] ነበረኝ። ያንን ምላስ ማውጭ ስከት ነፍስ ግቢ ነፍስ ውጪ ላይ ስለነበር እሱን ቀማኝ። እሱን ሲቀማኝ ያለኝ አማራጭ ጣቶቼን መክተት ነበር።”ብሩክ እንደሚያስረዳው 10 ሰከንድ እንኳ በማይፈጅ ጊዜ ልጁ ሕይወቱን ሊያጣ ይችል ነበር። ይሄ ነው ጣቶቹን ከትቶ ነብስ ለማዳን ይጥር የጀመረው።“ጥርሱን ዘግቶት ስላልነበር፤ እግዚአብሔርም ረድቶት ልጁ ተረፈ።”ብሩክ የፍራንክን ሕይወት ለማዳን ሲጥር ሁለቱም አውራ ጣቶች ጉዳት ደርሶባቸዋል።“ሁለቱም ጣቶቼ በጣም ተነከስዋል። ደም ሲፈስ ነበር። ትላንት ሕክምና ተደርጎልኝ አሁን ታሽገው ነው ያሉት” ይላል። በውድድሩ እየተሳተፉ ያሉ ሁሉም ክለቦች የሕክምና ባለሙያዎች አሏቸው። በሥፍራው የቀይ መስቀል አባላትም እንደነበሩ ብሩክ ያወሳል። ብሩክ ሕክምና የሰጠባቸው ጣቶቹ ታሽገው ብዙውን ጊዜ ሰዎች ምላሳቸውን ሲውጥ ሕክምና የሚያደርጉ ሰዎች ምን ዓይነት ሥልጠና አላቸው፤ ድፍረታቸውስ፤ አልፎም ሰው ለማዳን ያላቸው ቁርጠኝነት እንደሚወስነው ብሩክ ይናገራል።“ልጁ ሲወድቅ ብዙ ሰዎች ተረባርበዋል። ሰው እንዲህ ሲወድቅ ስታይ ስለሚያስደነግጥ ጭንቅላትህን ነው የምትይዘው። ፍራቻም አለ። የሰው ሕይወት እያለፈ ነው።”ለብሩክ ይህ የመጀመሪያው አይደለም። ከዚህ በፊት ሌሎች እንዲሁ ጉዳት ደርሶባቸው ራሳቸውን ሲስቱ እርዳታ ሰጥቷል። ይህኛው ግን ይለያል ይላል። እንዴት? “በጣም ጉልበት ነበረው። ምላስ ማውጫውን ‘ኪት’ ስከት መንትፎ ጣለብኝ። በጣም ከባድ ነበር። ድፍረቱም አልነበረኝም። ይሄ ልጅ ቢሞት፣ ሬሳው ሃገሩ ሲገባ፣ የሞተባት ከተማ. . . ብዙ ነገር እያሰብኩ ነበር። ነገር ግን በሰዓቱ እግዚአብሔር ኃይል ስለሰጠኝ ነው እጄን የከተትኩት። የሰው ሕይወት ከሚጠፋ የእኔ እጅ ቢቆረጥ ይሻላል።”ስታድየሙ ለ15 ደቂቃ ያክል ፀጥ ረጭ ብሎ እንደነበር ብሩክ ያስታውሳል። “የአምስት የአስር ሰከንድ ልዩነት ነው እንጂ በቃ ሞቶ ነበር” ይላል።“ከተቀመጥኩበት ተነስቼ ወደ ሜዳ እየሮጥኩ እስክገባ ቢያንስ 1 ደቂቃ ወስዶብኛል። ልጁ አወዳደቁ ያስታውቃል። ዝርግፍ ነው ያለው። ብዙ ባለሙያዎች ነበርን። ሮጠን ገባን። አፉን ሊዘጋ ሲል ነው ከእግዚአብሔር ጋር የደረስነው። ትረፍ ስትባል እንዲህ አይደል?” ምላስ መዋጥ ብዙውን ጊዜ በስፖርቱ ዓለም በተለይ በእግር ኳስ እንደሚጋጥም የሚናገረው ብሩክ ባለፈው ዓመት እንዲሁ ሁለት ጊዜ ተከስቶ እንደነበር ያስታውሳል። እሱ እንደሚያስረዳው ምላስ መዋጥ ተጫዋቾች በሰውነታቸው ያለው የምራቅ መጠን ዝቅ ብሎ ሳለ አየር ላይ በሚደርስ ግጭት የሚከሰት ነው።“ይህ ሲሆን መጀመሪያ የምናደርገው ይህ ሲሆን መጀመሪያ የምናደርገው ነገር ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች በጎናቸው ማስተኛት ነው። ምላስ አየር ላይ እንዲንጠለጠል ማለት ነው” ይላል ብሩክ።“ነገር ግን ይህን ለማድረግ ጉዳቱ ምን ያህል ነው የሚለው ይወስነዋል። ጉዳቱ ከባድ ከሆነ ወደ ጎን እስክታደርገው ድረስ ጥርሱን ከዘጋብህ በምንም ዓይነት መንገድ ማትረፍ አትችልም። ስለዚህ ሁለቱን ጉንጮች ከፍ በመያዝ ከፍ ማድረግ አለብን። ይህ አፍ የመዘጋት ዕድልን ይቀንሳል።”የሕክምና ባለሙያው ብሩክ ከደጋፊዎችና ከክለቡ ተጫዋቾች ከፍተኛ አድናቆት እንደተቸረው ይገልጣል። ለሲዳማ ቡና በሙያው ከማገልገሉ ባለፈ በሐዋሳ ከተማ የፊዚዮ ቴራፒ አገልግሎት የሚሰጠው ብሩክ ከየሥፍራው እየተቸረው ያለው አክብሮት ከፍተኛ እንደሆነ ይናገራል።“ስታድየሙ ፀጥ ብሎ ነበር። ሲመለስ [የልጁ ሕይወት] ከፍተኛ የሆነ ጭብጨባ ነበር። በኔና በሌሎች ማሕበራዊ ሚድያ ገፆች እጅግ በጣም ከፍተኛ አድናቆት ደርሶልኛል።እውነት ነው የምልህ የተቸረኝን አክብሮት አይቼ ማታ አልቅሻለሁ።“ክለቡ ሽንፈቱን ሁላ ረስቶ አቅፎኝ ደስታውን ሲገልፅ ነበር። በጣም ትልቅ ክብር ነው የሰጡኝ” ይላል።
ኢትዮ ካብ ስለሚሰጠው አገልግሎት ለማወቅ ድህረገጻችንን www.ethiocab.com ይጎብኙ
የ Customer application ለማውረድ http://user.ethiocab.com እንዲሁም የ Driver application ለማውረድ http://driver.ethiocab.com ያገኙናል