31 ጥቅምት 2023
አርጀንቲናዊው የኢንተር ማያሚ አጥቂ ሊዮኔል ሜሲ ለስምንተኛ ጊዜ የወንዶች ባለን ደ ኦር አሸናፊ ሆነ።የ36 ዓመቱ ሜሲ ባለፈው ዓመት በተካሄደው የኳታር ዓለም ዋንጫ ሃገሩን ለክብር በማብቃቱ ነው ፓሪስ በተካሄደው ሥነ–ሥርዓት እውቅና ያገኘው። እንግሊዛዊው የሪያል ማድሪድ አማካይ ጁድ ቤሊንግሃም ከ21 ዓመት በታች ለሆኑ ተጫዋቾች የሚሰጠውን ኮፓ ዋንጫ አንስቷል። ሊዮኔል ሜሲ ክብረ ወሰኑን ያራዘመበትን ባለን ደ ኦር ያነሳው የማንቸስተር ሲቲውን ኧርሊንግ ሃላንድን በማስከተል ነው። በዓለም ዋንጫ ፍፃሜ ሃት–ትሪክ በመሥራት በታሪክ ሁለተኛው ተጫዋች የሆነው ፈረንሳዊው ኪሊያን ምባፔ ሶስተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።“ለአንድ ተጨማሪ ጊዜ እዚህ መገኘት እና ይህን ታሪክ ማጣጣም ደስ የሚያሰኝ” ያለው ሜሲ፤ “የዓለም ዋንጫን ማንሳቴ እና ሕልሜን ማሳካቴ ደስተኛ አድርጎኛል” ሲል አክሏል። የቀድሞው የባርሴሎና እና የፓሪ ሳን ዠርማ የፊት መስመር ተጫዋች ጨምሮ ሁሉም የባለን ደ ኦር ሽልማቶች ልዩ ቦታ እንዳላቸው ተናግሯል።
ማንቸስተር ሲቲ ታሪክ በፃፈበት ባለፈው የውድድር ዘመን የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ፣ ቻምፒዮንስ ሊግ እና የኤፍ ኤ ዋንጫ ያነሳው፤ በ35 የሊግ ጨዋታዎች 36 ጎሎች ያስቆጠረው፤ በሁሉም ውድድሮች 52 ኳሶች ከመረብ ያገናኘው ሃላንድ ሜሲን በመከተል ሁለተኛ ሆኗል።ሃላንድ ለምርጥ ጎል አግቢዎች የሚሰጠውን የገርድ ሙለር ሽልማት ማንሳት ችሏል። ባለን ደ ኦር የዓመቱን ምርጥ እግር ኳስ ተጫዋች የሚመርጥ ሲሆን ከዓለም ዙሪያ የተውጣጡ 100 ጋዜጠኞች ናቸው ድምፅ የሚሰጡበት።
አርጀንቲና የዓለም ዋንጫ እንድታነሳ ያገዘው ሜሲ ክለቡ ኢንተር ማያሚ ሊግስ ካፕ የተሰኘውን ዋንጫ እንዲያነሳም ቁልፍ ሚና ተጫውቷል። ሜጀር ሊግ ሶከር የተባለውን የአሜሪካ ሊግ የተቀላቀለው ሜሲ በ14 ጨዋታዎች 11 ጎሎች አስቆጥሯል። ከሜሲ ቀጥሎ በርካታ ባለን ደ ኦር ያነሳው ፖርቹጋላዊው ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ሲሆን አምስት ጊዜ ሽልማቱን ተቀብሏል። ለሳዑዲ አረቢያው አል ናስር የሚጫዋተው ሮናልዶ ከፈረንጆ 2003 ጀምሮ ለመጀመሪያ ጊዜ የሽልማቱ ዕጩ ሳይሆን ቀርቷል። አርጀንቲናዊው ግብ ጠባቂ ኤሚሊያኖ ማርቲኔዝ የዓመቱ ምርጥ ግብ ጠባቂ ተብሎ ያሺን ትሮፊ የተሰኘውን ሽልማት አግኝቷል።
የእንግሊዙ ክለብ ማንቸስተር ሲቲ የዓመቱ ምርጥ ክለብ የተባለ ሲሆን የፔፕ ጉዋርዲዮላ ቡድን ባለፈው ዓመት ሶስት አብይ ዋንጫዎችን በማንሳት በእንግሊዝ ታሪክ ሁለተኛው ቡድን መሆኑ ይታወሳል። የሪያል ማድሪዱ ብራዚላዊ የክንፍ ተጫዋች ቪኒሲየስ ጁኒየር ዘረኝነትን ከእግር ኳስ ለማስወገድ በሠራው ሥራ የሶክራቲስ ሽልማት ተበርክቶለታል።
የባለን ደ ኦር ሽልማት ምርጥ 10
1. ሊዮኔል ሜሲ [አርጀንቲና / ፒኤስጂ / ኢንተር ማያሚ]
2. ኧርሊንግ ሃላንድ [ኖርዌይ / ማንቸስተር ሲቲ]
3. ኪሊያን ምባፔ [ፈረንሳይ / ፒኤስጂ]
4. ኬቪን ደ ብሩይነ [ቤልጂየም / ማንቸስተር ሲቲ]
5. ርድሪ [ስፔን / ማንቸስተር ሲቲ]
6. ቪኒሲየስ ጁኒየር [ብራዚል / ሪያል ማድሪድ]
7. ጁሊያን አልቫሬዝ [አርጀንቲና / ማንቸስተር ሲቲ]
8. ቪክተር ኦሲምሄን [ናይጄሪያ / ናፖሊ]
9. በርናንዶ ሲልቫ [ፖርቹጋል / ማንቸስተር ሲቲ]
10. ሉካ ሞድሪች [ክሮኤሺያ / ሪያል ማድሪድ]
ኢትዮ ካብ ስለሚሰጠው አገልግሎት ለማወቅ ድህረገጻችንን www.ethiocab.com ይጎብኙ
የ Driver application ለማውረድ http://driver.ethiocab.com እንዲሁም የ Customer application ለማውረድ http://user.ethiocab.com
ኑ አብረን ሰርተን ትርፋችንን እንካፈል !!