የዘንድሮው “የአሜሪካ ቁጥር 1 ታዳጊ ሳይንቲስት” ሽልማት አሸናፊ ትውልደ ኢትዮጵያዊው ሄማን በቀለ ነው።

ሄማን ለቆዳ ካንሰር ሕክምና የሚሆን ሳሙና በመሥራቱ ነው የዚህ ጉምቱ ሽልማት አሸናፊ የሆነው።

ላለፉት አራት ወራት የአሜሪካ ቁጥር አንድ ታዳጊ ሳይንቲስት ለመሆን ከሌሎች እኩዮቹ ጋር ሲፎካከር የነበረው ሄማን ለቆዳ ሕክምና የሚሆን ሳሙና በመፍጠር ከሌሎች ልቆ ተገኝቷል።

ይህ ውድድር ከአምስተኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎች ለውጥ ማምጣት የሚችል ፈጠራ እንዲሠሩ የሚያበረታታ ነው።

የዚህ ውድድር አሸናፊ የሆኑ ታዳጊዎች የ25 ሺህ ዶላር ሽልማትና ከፍተኛ እውቅና ያገኛሉ።

በቨርጂኒያ ግዛት የሚገኘው የዉድሰን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ9ኛ ክፍል ተማሪው ሄማን፤ 3ኤም እና ዲስከቨሪ ኤዱኬሽን የተሰኙት ተቋማት የሚያዘጋጁትን ሃገር አቀፍ ሽልማት አግኝቷል።

ግኝቱ እንዴት መጣ?

“እኔ የፈጠርኩት ለቆዳ ሕክምና የሚሆን ሳሙና ነው። ይህ ሳሙና የተለያዩ የቆዳ ካንሰሮችን ማከም የሚችል ነው” ሲል ሄማን ለቢቢሲ ይናገራል።

ሄማን እንደሚገልጠው ሳሙናው ለማከም የሚሆኑ የተለያዩ ነጥረ ነገሮችን የያዘ ሲሆን አልፎም ሳሙናው ቆዳችን ውስጥ ያሉ ካንሰርን መከላከል የሚችሉ ህዋሶችን (ሴሎችን) ያነቃቃል።

ሄማን የሠራው ሳሙና ከሌሎች የቆዳ ካንሰርን ከሚያክሙ ምርቶች ጋር ሲነፃፀር ዋጋው እጅግ ዝቅ ያለ ነው።

“ዋጋው 8 ዶላር ከ50 ሳንቲም ነው። የሌሎች የቆዳ ካንሰርን የሚያክሙ መድኃኒቶች ዋጋ በአማካይ 40 ዶላር ነው” ይላል ሄማን።

የቆዳ ካንሰር አሜሪካ ውስጥ ከሁሉም የካንሰር ዓይነቶች በላይ የተስፋፋ ነው። ሃገሪቱ በየዓመቱ ለቆዳ ካንሰር ሕክምና 8.1 ቢሊዮን ዶላር ወጭ ታደርጋለች።

“መጀመሪያ አስቤ የነበረው የቆዳ ካንሰርን የሚያጠፋ ሳሙና ለመሥራት ነበር። ከተለያዩ ሳይንቲስቶችና አጥኚዎች ጋር ከመከርኩ በኋላ አንዳንድ ለውጦችን ባደርግ የቆዳ ካንሰርን መከላከል ብቻ ሳይሆን ማከም እንደሚችል ተረዳሁ።”

ኢትዮጵያ ምን ተመለከተ?

ኢትዮጵያ የተወለደው ሄማን ሃገር ቤት የተመለከታቸው ነገሮች በሳይንስ ዘርፍ አንድ ለውጥ የሚያመጣ ምርት ለመሥራት እንዳነሳሱት ይናገራል።

“ኢትዮጵያ እያለሁ የተለያዩ ነገሮችን እመለከት ነበር። ሰዎች ፀሐይ እየመታቸው ለረዥም ሰዓታት ሲሰሩ አያለሁ። በድኅነት ምክንያት ሰዎች የጤና አገልግሎት በቀላሉ ማግኘት እንደማይችሉ ተመልክቻለሁ። ይህ የበርካታ የዓለማችን ሃገራት እውነታ ነው።”

ልጅ ሳለሁ ያልተረዳኋቸው አሁን እየገቡኝ የመጡ እውነታዎች አሉ የሚለው ሄማን መድኃኒቶች ለሁሉም ተደራሽ መሆን አለባቸው ሲል ይከራከራል።

“አሁን የተረዳሁት ነገር በሽታን ለመከላከል የሚሆኑ የምናመርታቸው መድኃኒቶች ውጤታማ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም የሚደርሱ መሆን እንዳለባቸው ነው። በዚህ ምክንያት ነው የሠራሁት የቆዳ ካንሰርን የሚያክም ሳሙና ውጤታማ ብቻ ሳይሆን ዋጋው ተመጣጣኝ እንዲሆንም የፈለግኩት” ይላል።

“ቅድሚያ የምሰጠው ነገር ይሄ ነው። ሳይንስ ለሰው ልጆች እኩል ጥቅም ላይ መዋል አለበት። ሳይንስ በጣም እወዳለሁ። ከዚያም በላይ ሳይንስ ለዓለማችን ችግሮች መፍትሔ ሲሆን ማየት ያስደስተኛል። የኔ ሥራ ወደታች ወርዶ ለውጥ ማምጣት ቢችል ደስ ያሰኘኛል።

የቆዳ ካንሰር ሕክምና ከዚህም ቀደም የነበረ ነው። ቀዶ ጥገናም ሆነ ራዲየሽን ቴራፒ ከዚህ ቀደም ነበሩ። ነገር ግን ይህ አማራጭ ለሁሉም ተደራሽ አይደለም። እኔ ትልቁ ትኩረቴ የነበረው እሱ ነው።”

የወደፊት ዕቅድ

ሄማን ወደፊት ሊያሳካቸው የሚልፈጋቸው በርካታ ሐሳቦች ቢኖሩትም ለጊዜው ቅድሚያ መስጠት የሚፈልገው ግኝቱን ማሳደግ ነው።

“የኔ ሥራ ለዚህ ሽልማት ፕሮጀክት ብቻ ጥቅም እንዲውል ብቻ ሳይሆን ለመላው ዓለም እንዲሰራጭ እፈልጋለሁ” የሚለው ለዚህ ነው።

“ይህ የሳይንስ ምርምር ብቻ ሆኖ እንዲቀር አልፈልግም። የኤፍዲኤ [የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር] ማረጋገጫ ለማግኘት ሰዎች ላይ ሙከራ ማድረግ አለብኝ። አልፎም በ2028 [በአውሮፓውያኑ] ይህን ፕሮጀክት ለትርፍ ያልተቋቋመ ‘ፋውንዴሽን’ ማድረግ እሻለሁ። መድኃኒቱ ለሁሉም መዳረስ አለበት ብዬ አምናለሁ።”

ሄማን በዕቅድ እና በዝግጅት የሚያምን እንደሆነ ይገልጣል።

“በዕቅድ አምናለሁ። ሁሉን ነገር ማሳካት ከባድ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን የአቅሜን ማድረግ አለብኝ። ከተቻለ ከ2028 በፊት ሁሉን ማሳካት ነው ሕልሜ። የረዥም ጊዜ ዕቅዴ ግን በ2028 ይህ ማሳካት ነው።”

ሄማን ሽልማት እና እውቅና ካስገኘለት የምርምር ውጤት ባለፈ በሌሎች የሳይንስ መስኮች የራሱን አሻራ ማሳረፍ ይፈልጋል።

ለሳይንስ ያለኝ ፍቅር ጥልቅ ነው የሚለው ሄማን ወደፊት ምን ማድረግ እሻለሁ የሚለውን ጥያቄ ገና አለመመለሱን ያስረዳል።

“ባለፈው ዓመት ምን ማጥናት ትፈልጋለህ ብለህ ብትጠይቀኝ ኖሮ ኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ (የኤሌክትሪክ ምህንድስና) ነበር የምለው። ነገር ግን ከዚህ ፕሮጀክት በኋላ ወደ ባዮ ሜዲካል ዘርፍ እያደላሁ ነው። ምናልባት በሚቀጥለው ዓመት በዘረ መል ምርምር ልታገኘኝ ትችል ይሆናል። የማውቀው ነገር ቢኖር ለሳይንስ ያለኝን ፍቅር ነው። “ ሲልም ታዳጊው ከቢቢሲ ጋር በነበረው ቆይታ ተናግሯል።

ኢትዮ ካብ ስለሚሰጠው አገልግሎት ለማወቅ ድህረገጻችንን www.ethiocab.com ይጎብኙ

Driver application ለማውረድ http://driver.ethiocab.com እንዲሁም Customer application ለማውረድ  http://user.ethiocab.com     

አብረን ሰርተን ትርፋችንን እንካፈል  !!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *