![](https://ethiocab.com/wp-content/uploads/2023/10/istockphoto-1194692009-612x612-1.jpg)
![](https://ethiocab.com/wp-content/uploads/2023/10/istockphoto-1327074549-612x612-1.jpg)
![](https://ethiocab.com/wp-content/uploads/2023/10/istockphoto-133910422-612x612-1.jpg)
ዌንዲ ሀል ካናዳዊ የእንቅልፍ አጥኚ ናቸው። ከስምንት ዓመት በፊት 235 ቤተሰቦችን ያማከለ ጥናት ሠርተዋል። ጥናቱ ልጆችን መተኛት ማስተማር ላይ ያተኮረ ነበር። ከስድስት እስከ ስምንት ወር የሆናቸው ሕጻናትን አሳትፏል።ቤተሰብ ልጆቹን ሳያባብል ልጆቹ በራሳቸው እንቅልፍ እንዲወስዳቸው ማድረግን ይዳስሳል። ወላጆች የተለያየ መንገድ በመጠቀም ልጆቻቸውን ያስተኛሉ። ልጆቹን ሳያባብሉ ለማስተኛት የሚጠቀሟቸው መንገዶችም አሉ። ልጆች ከተኙ በኋላ ሲነቁ ሳያባብሏቸው ልጆቹ ተመልሰው እንዲተኙ ማድረግንም ያካትታል። አንዳንድ ወላጆች ልጃቸውን የሚያባብሉበትን የጊዜ ክፍተት ይወስናሉ። ልጆች ሲያለቅሱ ሳያባብሉ የሚተዋቸውም አሉ። ይህ በሁሉም አገር የሚዘወተር አይደለም። ለምሳሌ የአሜሪካ እናቶች ከልጃቸው በተለየ ክፍል ሲተኙ ለማያን እናቶች ይህ የሚታሰብ አይደለም። ልጆች በአግባቡ ሳይተኙ መቅረታቸው ወይም ደጋግመው ከእንቅልፍ መነሳታቸውን እናቶች ከሚገጥማቸው ድብታ ጋር የሚያያይዙ አሉ። ከአሥር የአሜሪካ መጻሕፍት ስድስቱ ልጆች ሲያለቅሱ አታባብሉ ይላሉ። በካናዳ፣ አውስትራሊያ፣ ስዊዘርላንድ እና ጀርመን ያሉ ቤተሰቦችም ይህንን መንገድ ይከተላሉ። ወላጆች ልጆቻቸውን መተኛት የሚያስተምሩበትን መንገድ የሚጠቁሙ መጻሕፍትና ጥናቶች በርካታ ናቸው። የዌንዲ ጥናት እንደሚያመለክተው፣ ልጆቻቸውን እንዴት ማስተኛት እንደሚችሉ መመሪያ የተሰጣቸው ወላጆች በተሻለ ሁኔታ ልጆቻቸውን ያስተኛሉ። ልጆቹ ዘለግ ላለ ጊዜ ይተኛሉ፤ ከእንቅልፍ የሚነሱበት ጊዜም ያጥራል። የሕጻናት ሐኪሞች በተለይ በአሜሪካ እና አውስትራሊያ ልጆችን መተኛት ማሠልጠንን ሲደግፉ የሕጻናት አእምሮ ጤና ባለሙያዎች እምብዛም አይደግፉትም። በጉዳዩ የሚሠሩ ጥናቶች በየጊዜው ውጤታቸው አዳዲስ ነገር ያሳያል። አንዳንድ ቤተሰብ ልጁ ከመተኛቱ በፊት ትንሽ እንደሚያለቅስ ወይም ከነጭራሹ እንደማያለቅስ በመግለጽ ልጁን መተኛት ማሠልጠን አስፈላጊነቱ አይታየውም። ለዚህ ጥናት የሚመረጡ ቤተሰቦች ጥናቱ መሀል ላይ ማቋረጥና የእንቅልፍ ጉዳይ በቀላሉ ለመረዳት የተመቸ አለመሆኑ ምርምሩን ፈታኝ ያደርጉታል። ልጆች ከእንቅልፋቸው ሲነቁ እንዳያለቅሱ ማስተማር ከተቻለ፣ ወላጆቻቸውን በለቅሶ አይቀሰቅሱም። ያ ማለት ደግሞ ወላጆች ልጆቹ ተኝተው እንዳደሩ ያስባሉ ማለት ነው። እነዚህ ጥናቶች ወላጆች በሚሰጡት ምላሽ እና በወላጆች ምልከታ ላይ መመሥረታቸውም ጥናቱን ፈታኝ ያደርገዋል። በዌንዲ ጥናት፣ ወላጆች ልጆቻቸውን ለተወሰነ ጊዜ አባብለው ለተወሰነ ጊዜ እንዲተዋቸው ይደረጋል። የሚያባብሉበትና የሚተውበት ሰዓት ተመጣጣኝ እንዲሆን ይነገራቸዋል።ልጆች ሲያለቅሱ ልጆቹ ካሉበት ክፍል የሚወጡና እዛው ክፍል ውስጥ ሆነው ከማባበል የሚታቀቡም አሉ።ይህንን ሥልጠና የወሰዱ ቤተሰቦች ልጆች ዘለግ ላለ ጊዜ እንደተኙ የዌንዲ ጥናት ይጠቁማል።“ከሠለጠኑት ልጆች መካከል ከእንቅልፋቸው ቢነቁም ወላጆቻቸውን ያላነቁ ሕጻናት አሉ” ይላሉ አጥኚዋ። የእንቅልፍ ቆይታን የሚመዘግብ መሣሪያ ተጠቅመው ባገኙት ውጤት፣ ሥልጠና የተሰጣቸው ልጆች እንቅልፍ ከ188 ደቂቃ ወደ 204 (በ8.5%) መሻሻሉን ደርሰውበታል። ልጆቻቸው አልቅሰው ያልቀሰቀሷቸው ቤተሰቦች የተሻለ እንቅልፍ ማግኘታቸውንና አለመዳከማቸውን ገልጸዋል።በተለያዩ አገራት በተሠሩ ጥናቶች እናቶች የሚያማክራቸው ሰው ሲያገኙ የተሻለ ስሜት እንደተሰማቸው ጠቁመዋል። ብዙ ዘመነኛ ቤተሰቦች ውስጥ እናትም አባትም ሥራ ስላላቸው በቂ ጊዜ አያገኙም። ማታ ለመተኛት ሲሉ ልጆቻቸው እንዳይነቁ የተለያዩ መንገዶች ለመጠቀም የሚገደዱትም ለዚሁ ነው። ልጆችን እንቅልፍ ማሠልጠን ውጤት ያሳያቸው ቢኖሩም፣ ልጆቻቸው በራሳቸው ጊዜ እንቅልፍን የተለማመዱላቸውም አሉ። ከ4,000 በላይ ልጆችን ያሳተፈ ጥናት እንደሚያሳየው፣ 71% የሚሆኑ በየጊዜው ይነቁ የነበሩ የአምስት ወር ሕጻንት 20 ወር ሲሆናቸው ተሻሽለዋል። 89% የሚሆኑት ደግሞ 4.5 ዓመት ገደማ ሲሆናቸው ለውጥ አሳይተዋል። አጥኚዎች እንደሚሉት፣ ወላጆች ሥልጠናውን መስጠት አስፈላጊ ነው ብለው ካመኑ ብቻ ነው ማከናወን ያለባቸው። ችግሩ ባለበት ሁኔታ ብቻ የተሻለ ነው ተብሎ የታመነውን መንገድ ወላጆች እንዲከተሉም አጥኚዎች ይመክራሉ።
የሚወጡ አዳዲስ መረጃዎችን ለማግኘት ድህረገፃችንን ይጎብኙ እንዲሁም ኢትዮ ካብ ስለሚሰጠው አገልግሎት ለማወቅ ድህረገፃችንን www.ethiocab.com ይጎብኙ !!
የ Driver application ለማውረድ http://driver.ethiocab.com እንዲሁም የ Customer application ለማውረድ http://user.ethiocab.com
ኑ የእኛንም የልጆቻችንንም ጤና እየጠበቅን አብረን ከኢትዮ ካብ ጋር የትርፍ ተካፋይ እንሁን !!