![](https://ethiocab.com/wp-content/uploads/2023/09/003681f0-4969-11ee-adca-f9ef480aa1c2.jpg.webp)
![](https://ethiocab.com/wp-content/uploads/2023/09/072511c0-40cc-11ee-a3f7-5f0c850698a6.jpg.webp)
ፕሮፌሰር ወንድማገኝ እምቢአለ በቅርቡ በሲንጋፖር ዓለም አቀፍ የቆዳ ሕክምና ባለሙያዎች ጉባኤ ተካሂዶ ነበር። በጉባኤው ላይ 11500 የሚሆኑ የቆዳ ሐኪሞች እና መድኃኒት አምራቾች ተገኝተዋል። በዚህ ጉባኤ ላይ ከቆዳ ሕክምና ጋር በተያያዘ ማኅበረሰብ ላይ ለውጥ ማምጣት የሚያስችሉ ሥራዎችን በመሥራት በተካሄደ ዓለም አቀፍ ውድድር ከመካከለኛው ምሥራቅ እና ከአፍሪካ ፕሮፌሰር ወንድማገኝ እምቢአለ አሸናፊ ሆነዋል። በውድድሩ በሰሜን አሜሪካ፣ በደቡብ እና መካከለኛው አሜሪካ፣ በአፍሪካ እና በመካከለኛው ምሥራቅ፣ በእስያ እና በአውሮፓ ምድብ የሚገኙ የዘርፉ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።
ለውድድሩም ከ66 አገራት 193 የፕሮጀክት ሃሳቦች ቀርበው ነበር። ከእነዚህ መካከል ነው ፕሮፌሰር ወንድማገኝ ያቀረቡት ሃሳብ በመካከለኛው ምሥራቅ እና በአፍሪካ የሚገኙ ባለሙያዎች ካቀረቡት መካከል አሸናፊ ሆኖ የተመረጠው። ፕሮፌሰር ወንድማገኝ ሽልማቱን የተቀዳጁት በተለይ የዝሆኔ (Podoconiosis) እና ቆንጭር ወይም ሻህ (Cutaneous leishmaniasis) የተባሉት በሽታዎች ሕክምና ወደ ማኅበረሰቡ ለማድረስ በሚያስችል ፕሮጀክት ነው። ፕሮጀክቱን የሰሩት በሰሜን እና በደቡብ የኢትዮጵያ ክፍል የዝሆኔ በሽታ ሕክምና የሚሰጡ ድርጅቶች ሕክምናውን ማዕከላዊ ለማድረግ ካቋቋሙት ናሽናል ኔትወርክ ፎር ፖሎ (ናፓን) ጋር በመሆን ሲሆን፣ ይህንን ዓላማ የሰነቀውን ፕሮጀክት ያስፈጸሙበት ዘንድም የ20 ሺህ ዩሮ የገንዘብ ድጋፍ ተበርክቶላቸዋል።
የዝሆኔ በሽታ ምንድን ነው?
የዝሆኔ በሽታ ከፍተኛ የእግር እብጠት የሚያስከትል ነው። ከእብጠቱ ጋር በተያያዘ በየጊዜው ትኩሳት፣ ራስ ምታት እና ብርድ ብርድ የማለት፣ የማንቀጥቀጥ እና የማቅለሽለሽ ህመም ያመጣል። በሽታው እየከፋ ሲሄድም ቁስል እና መጥፎ ጠረንን ያስከትላል።በዚህም የተነሳ ህሙማኑ በማኅበረሰቡ ይገለላሉ። በአማራ፣ በወላይታ፣ በኦሮሚያ እና በመካከለኛው ደቡብ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ሕይወትን የሚገፉና በባዶ እግራቸው የሚሄዱ አርሶ አደሮች በአብዛኛው በዚህ በሽታ ይጠቃሉ። ይሁን እንጂ በሽታው በኢትዮጵያ ውስጥ ትኩረት ተነፍጎት ቆይቷል። አሁንም የሚሰጠው ትኩረት እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። በዚህም ምክንያት በቀላል ሕክምና እና ቅድመ ጥንቃቄ ሊድን እንዲሁም መከላከል የሚቻለው ይህ በሽታ የበርካቶችን ሕይወት አናግቷል።ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በዚህ በሽታ የተጠቁ 1 ሚሊዮን ሰዎች በኢትዮጵያ ውስጥ ይኖራሉ። 35 ሚሊዮን የሚሆን ሕዝብ ደግሞ ለበሽታው ተጋላጭ እንደሆነ ይታመናል።
“ዛሬ የደስታዬ ቀን ነው፤ በልጄ ሠርግ ላይ ተገኘሁ” አቶ ብርሃኑ የዝሆኔ በሽታ ተጠቂ ናቸው። ለዓመታት በበሽታው ሲሰቃዩ ነው የቆዩት። ከቤተሰባቸው ሳይቀር መገለል ደርሶባቸዋል። ያልተጠየፋቸው የለም። ከቤተሰቦቻቸው ተነጥለው የራሳቸው ጎጆ ውስጥ እየዋሉ እያደሩ ሕይወትን ገፍተዋል። አቶ ብርሃኑን የፕሮፌሰር ወንድማገኝ ታካሚ ናቸው። በሽታው የጀመራቸው የዛሬ 20 ዓመት አካባቢ ነው። በሙያቸው ነጋዴ ሲሆኑ፣ ከሚኖሩበት ዱር ቤቴ ከተማ 60 ኪሎ ሜትር ገደማ ወደምትርቀው ባሕር ዳር በእግራቸው እየሄዱ የንግድ ሥራቸውን ይከውኑ ነበር። በወቅቱ በአካባቢው የትራንስፖርት አገልግሎት አልነበረም። የዛሬ 20 ዓመት አካባቢ የትራንስፖርት አገልግሎት ሲጀምር ለንግድ ሥራ ወደ ባሕር ዳር ለማቅናት ሎንችና (አነስተኛ አውቶብስ) ላይ ተሳፈሩ።ሎንችናው ተሳፋሪ ሲጠብቅ ፀሐዩ ከረረ። እግራቸው መሽተት ጀመረ። መኪና ውስጥ የተሳፈሩት ሰዎች አፍንጫቸውን መያዝ ጀመሩ። የመኪናው ሹፌርም ዞር ብሎ “አንተ ልጅ ምንድን ነው? የሞተ አይጥ ጭነሃል እንዴ?” ሲል ጠየቀ። አቶ ብርሃኑ በሃፍረት አንዳች ነገር ሰውነታቸውን ወረረው።“ያኔ ምድር ተከፍቶ ቢውጠኝ ደስታውን አልችለውም ነበር” ይላሉ አጋጣሚውን ሲያስታውሱ። እርሳቸው ብቻ ሳይሆኑ በአካባቢው የሚያውቃቸው የመኪናው ረዳትም በሹፌሩ ንግግር ሲሸማቀቅ ተመለከቱት። ይህንን መቋቋም ያልቻሉት አቶ ብርሃኑ ምንም ሳይናገሩ ከተሳፈሩበት መኪና ወረዱ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በመኪና ተሳፍረው አያውቁም። ንግዳቸውንም ልጆቻቸው እንዲያስቀጥሉት ሰጡ። ቤተ ክርስቲያን እያስቀደሱ ደጀ ሰላም በር ላይ እየዋሉ መኖር ጀመሩ። ሁለት ሦስት ዓመታትን በዚህ መልኩ ገፉ። ይህም ግን ከመገለል አልታደጋቸውም። ብዙም ሳይቆይ የገዛ ቤተሰቦቻቸውም አማረሩ። ከቤታቸውም ጓሮ ለብቻቸው ጎጆ ቤት ሰሩላቸው። ከዚያን ቀን ጀምሮ አንድም ቀን ሠርግ፣ ማኅበር፣ ሰንበቴ እና ማኅበራዊ ክንውኖች ላይ ተሳትፈው አያውቁም። ቤታቸው እንኳን ድግስ ሲዘጋጅ የሚበላውም፣ የሚጠጣውም የሚመጣላቸው እዚያው ለብቻቸው ከተሰራችው ጎጆ ነው። ከዚህ ቀደም ልጆቻቸውን ሲድሩ ሠርጋቸው ላይ አልተገኙም። በዚህ የማይታገሉት ፈተና ውስጥ ሳሉ ነበር ፕሮፌሰር ወንድማገኝ በከፈቱት የሕክምና ማዕከል ሕክምናውን የማግኘት ዕድል ያገኙት። ሕክምናውን ካገኙ በኋላ ግን እግራቸው መሽተቱን አቆመ። ወደ ቀደመው ሕይወታቸው ተመለሱ። ሌላኛ ልጃቸውንም ዳሩ። ሠርጉም ላይ ተገኝተው ወዳጅ ዘመድን አስተናገዱ። ሕክምናውን በጀመሩ በሦስተኛ ወራቸውም “ዛሬ የደስታዬ ቀን ነው። ልጄን ዳርኩ፤ የልጄ ሠርግ ላይም ተገኘሁ” ሲሉ ታሪካቸውን ላከፈሉን ፕሮፌሰር ወንድማገኝ ምስጋናቸውን አቀረቡ።
ፕሮፌሰር ወንድማገኝ እምቢአለ የቆዳ እና የአባላዘር በሽታ ሐኪም እንዲሁም በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ናቸው። የቆዳ ሐኪም ሆነው ሥራ ከጀመሩ በኋላ የዝሆኔ በሽታ ሕክምና በጤና ተቋማት አይሰጥም ነበር። በዚህ በሽታ የተጠቁ ሰዎችም ፈውስን ለማግኘት የነበራቸው ብቸኛው አማራጭ ወደ እምነት እና የፀበል ቦታዎች መሄድ ነበር። በወቅቱ የሕክምና አገልግሎቱ የሚሰጠው ሃይማኖት ነክ በሆኑ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ብቻ ሲሆን፣ ይህም በደቡብ ክልል፣ ሶዶ ውስጥ ብቻ ነበር የሚገኘው። “በሽታው በኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ሰዎችን ቢያጠቃም ትኩረት ተነፍጎት የቆየው ነው” ይላሉ ፕሮፌሰር ወንድማገኝ። በዚህም ምክንያት ስለበሽታው በዓለም አቀፍም ሆነ በአገር አቀፍ ደረጃ ያሉት መረጃዎች እምብዛም አልነበሩም። ይህ ያሳሰባቸው ሐኪሙ ሕክምናውን በሰሜን ኢትዮጵያ ክፍል ለማስጀመር በወቅቱ ኢንተርናሽናል ኦርቶዶክስ ቸርች ቻሪቲ ከሚባል ማኅበር ጋር በመተባበር በደብረ ማርቆስ ከተማ አገልግሎቱ እንዲጀመር አደረጉ። እርሳቸውም በበጎ ፈቃደኝነት በሙያቸው ማገልገል ጀመሩ። ፕሮፌሰር ወንድማገኝ እንደሚሉት የዝሆኔ በሽታ ሕክምናው ቀላል ቢሆንም ትኩረት ስለተነፈገው በርካቶችን ለስቃይ እና ለማኅበራዊ መገለል ዳርጓል። ሕክምናው እግርን ማጠብ፣ ቅባት መቀባት፣ እግር ላይ ያሉ ቁስሎችን ማከም እና በፋሻ ማሰር እንዲሁም ጫማ ማድረግ ነው። ይህ ቀላል ሕክምና በታማሚዎች ላይ ትልቅ ለውጥ ለማምጣት ቢያስችልም፣ በወቅቱ የጤና ባለሙያዎችም እውቀቱ ስላልነበራቸው አገልግሎቱ በጤና ተቋማት አይሰጥም ነበር። “በሽታው በአገር አቀፍ ደረጃ እንዲታወቅ እና በቆላማ አካባቢ ትኩረት ከተነፈጉ በሽታዎች ውስጥ ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ አካል እንድትሆን የተካተተችው ካለፉት 15 ዓመታት ወዲህ የተለያዩ ተመራማሪዎች እና በጎ አድራጎት ድርጅቶች በሠሩት ሥራ ነው” ይላሉ ፕሮፌሰሩ። ፕሮፌሰሩ ከደብረ ማርቆሱ ማዕከል በመቀጠል ዱርቤቴ ላይ የሕክምና ማዕከል ከፍተው አገልግሎት መስጠት ጀመሩ። በዚህም ታካሚዎቹ የቀዶ ጥገና አገልግሎት እንዲያገኙ አስችለዋል። በዚህም ቆዶ ሕክምናው ለውጥ እንዳመጣላቸው ሳይንሳዊ የሆነ ጥናቶችን አካሂደዋል። እርሳቸው እንደሚሉት እነዚህ ሳይንሳዊ ጥናቶች ቀዶ ሕክምናው የሕክምናው አካል እንዲሆን ጤና ጥበቃ ፕሮግራሙ ውስጥ እንዲያካትተው በር ከፍተዋል። ሆኖም ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የዝሆኔ በሽታ በአገር አቀፍ ደረጃ በቆላማ አካባቢዎች ትኩረት ከሚሹ በሽታዎች ውስጥ ቢያካትተው እና መመሪያዎችን ቢዘጋጅም፣ አሁንም ድረስ ሕክምናው በጤና ጣቢያዎች አይሰጥም። በዚህም ምክንያት ነው ፕሮፌሰር ወንድማገኝ እምቢአለ፣ በቀላል ሕክምና ሊድን በሚችል በሽታ የሚሰቃዩ ሰዎችን ለመታደግ ሲሉ በሽታው ላይ ትኩረት አድርገው መሥራት የጀመሩት። አሁን ቀርጸው እየሠሩበት ባለው ፕሮጀክትም የጤና ባለሙያዎችን በማሠልጠን ታካሚዎች በያሉበት ቦታ አገልግሎቱን እንዲያገኙ ለማስቻል አልመዋል። ፕሮፌሰር ወንድማገኝ በዚሁ የማኅበረሰብ አገልግሎት ተግባራቸው የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሰኔ ወር ላይ 60ኛ ዓመቱን ሲያከብር ተሸላሚ ሆነዋል። በ2011 ዓ.ም በሴዑል በተካሄደው የዓለም የቆዳ ሐኪሞች ኮንግረንስ ላይ ጀማሪ የቆዳ ሐኪም ሳሉ ከኤችአይቪ ታካሚዎች ጋር በተያያዘ በሠሯቸው በጎ ሥራዎች የገንዘብ ሽልማት የተበረከተላቸው ሲሆን፣ በስብሰባው ላይ እንዲሳተፉም ዕድል አግኝተዋል።
በሸታው ለመጀመሪያ ጊዜ የታወቀው እና ስያሜውን ያገኘው በ1970ዎቹ በኢትዮጵያ ውስጥ ነው።
በሽታው አብዛኛውን ጊዜ በመሬት ቁፋሮ ሥራ ላይ የተሰማሩ እና ባዶ እግራቸውን የሚሄዱ ገበሬዎችን እንደሚያጠቃ ከታወቀ በኋላ ዓለም አቀፍ ጥናቶች ተካሂደዋል። ከዚያም በተለይ በካሜሮን፣ በታንዛኒያ፣ በሩዋንዳ በሽታው እንዳለ ታወቀ። አንዳንድ ምልከታዎችም 17 በሚሆኑ የዓለም አገራት ውስጥ በሽታው እንዳለ አመልክተዋል። ከፍተኛ የበሽታው ተጠቂዎች ቁጥር ያለው ግን በኢትዮጵያ ውስጥ ነው። ከ1970ዎቹ በኋላ ለ30 ዓመታት እዚህ ግባ የሚባል ጥናት አልነበረም። ከ2000 ዓ.ም. በኋላ ግን አንዳንድ ተመራማሪዎች ጉዳዩን አንስተው እንደገና ጥናት ማድረግ ጀመሩ። በ2007 ዓ.ም. ላይ በተሰራ አንድ አገር አቀፍ ጥናትም 1.5 ሚሊዮን ሰዎች በሽታው እንዳለባቸው ያመለከተ ሲሆን፣ ከ35 አስከ 50 ሚሊዮን የሚሆኑ ገበሬዎች ለዚህ በሽታ የተጋለጡ መሆናቸውን አመልክቷል።
ኢትዮ ካብ በሀገራችን ልጅ በመጣው ድል የተሰማውን ደስታ ሲገልፅ በታላቅ ክብር ነው !! እንኳን ለአዲሱ አመት አደረሳችው ይለናል!!
ኢትዮ ካብ ስለሚሰጠው አገልግሎት ለማወቅ ድህረገፃችንን www.ethiocab.com ይጎብኙ
የ Customer application ለማውረድ http://user.ethiocab.com እንዲሁም
የ Driver application ለማውረድ http://driver.ethiocab.com ያገኙናል